ናይጄሪያ የታገቱ ሴት ተማሪዎችን ለማስለቀቅ ከቦኮሃራም ጋር ልትደራደር ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የናይጄሪያ መንግስት በአሸባሪው ቡድን ቦኮሃራም የታገቱ ሴት ተማሪዎችን በድርድር ለማስለቀቅ ማቀዱን አስታወቀ።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2014 እና ባለፈው ወር የታገቱትን ሴት ተማሪዎች ለማስለቀቅ መታቀዱ የተነገረው ከአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቴለርሰን ጋር ውይይት ከተካሄደ በኋላ ነው።

 የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሙሀሙድ ቡሃሬ ድርድሩ አስፈላጊነት መሆኑን የገለፁ ሲሆን ፥ በቺቦክ እና ዳፕቺ አካባቢዎች በቦኮሃራም የታገቱ ሴቶችን

ለመመለስ ከወታደራዊ ዘመቻ ይልቅ ድርድር መመረጡን ፕሬዘዳንቱ ተናግረዋል።

የታገቱ ሴቶችም አካላዊ ጥቃት ሳይደርስባቸው እንዲለቀቁ ለማድረግ ከአለም አቀፍ ተቋማት እና ከተደራዳሪዎች ጋር እንደተሰራም ተነግሯል።

ቦኮሃራም ባለፈው ወር በዮቤ ግዛት በምትገኘው ዳፕቺ በተባለች ከተማ በርካታ ሴት ተማሪዎች ባገቱበት ወቅት በርካቶችም ከእገታው መትረፋቸው ይታወሳል።

በቺቦክ ግዛት ቦኮሃራም በ2014 270 ሴት ተማሪዎችን ያገተ ሲሆን፥ መንግስት ክፋያ በመፈፀም በርካቶችን ማስለቀቅ ቢችልም በአሁኑ ወቅት ከ100 በላይ ታግተው ይገኛሉ ተብሏል።

የናይጄሪያ መንግስት አሸባሪው ቡድን ቦኮሃራምን ለማጥፋት በሚያደርገው ትግል አሜሪካ ለምታደርገው ድጋፍ ምስጋና አቅርቧል።

የሽብር ቡድኑ በሀገሪቱ ጥቃት ማድረስ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በትንሹ 20 ሺህ ሰዎች መሞታቸው ይነገራል።

ምንጭ፦ ፕሬስ ቲቪ