ማረጋገጫ ለማግኘት ወደ ባለስልጣኑ ከሚሄዱ መንጃ ፍቃዶች ውስጥ ግማሽ ያህሉ ሀሰተኛ መሆናቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌዴራል የትራንስፖርት ባለስልጣን የመንጃ ፍቃዳቸው ትክክለኝነት እንዲረጋገጥላቸው ከሚመጡ አሽከርካሪዎች መካከል ግማሽ ያህሉ የሀሰት መንጃ ፍቃድ መሆኑን አስታወቀ።

ሀገሪቱ በትራፊክ አደጋ ምክንያት በየአመቱ ከ4 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎችን እና ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረትን ታጣለች።

ለዚህም ለአሽከርካሪዎች የትራፊክ አደጋ መነሻ የብቃት አለመኖርና ህጋዊ ባልሆነ መንጃ ፍቃድ መንቀሳቀሳቸው ነው።

ይህም በአማራ ክልል በተያዘው አመት በተደረገው ቁጥጥር አጠራጣሪ ሆነው ከተያዙት 278 አሽከርካሪዎች ውስጥ 91ዱ አሽከርካሪዎች መንጃ ፍቃዳቸው ሀሰተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

ሌሎች 20 የሚሆኑት ደግሞ መንጃ ፍቃድ ሳይኖራቸው ሲያሽከረክሩ የነበሩ መሆናቸውን ነው የክልሉ የመንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊው አቶ ጃንጥራር አባይ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት።

ሌላው የሀሰት የመንጃ ፍቃድን ይዞ ማሽከርከር ስጋት የሆነበት የደቡብ ክልልም ቢሆን፥ በርካቶች በዚህ መልኩ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አሽከርካሪዎችን መያዙን ይፋ አድርጓል።

በዚህም በክልሉ በተለያዩ ጥፋቶች ተይዘው ፍተሻ ከተደረገባቸው 292 አሽከርካሪዎች ውስጥ፥ 108 አሽከርካሪዎች በሀሰተኛ መንጃ ፍቃድ ሲያሽከረክሩ የተገኙ እና አደጋም ያደረሱ መሆናቸውን የክልሉ የመንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ስኳሬ ሹዳ ገልፀዋል።

በሌላ በኩል የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ሀይለማሪያም እንደገለፁት፥ ወደ ባለስልጣኑ መንጃ ፍቃድቸው እንዲረጋገጥ ከሚመጡት ውስጥ ግማሽ ያህሉ ሀሰተኛ መንጃ ፍቃድ ይዘው ይገኛሉ።

ዳይሬክተሩ በአዲስ አበባም በዚህ አመት ባለፉት ወራት በተደረገው ፍተሻ 24 በመቶ ያህል ሀሰተኛ መንጃ ፍቃድ መገኘቱን እና ሌሎች ክልሎችም ላይ የተገኙ ህጋዊ ያልሆኑ መንጃ ፈቃዶች እንደ ማሳያነት ያነሳሉ።

ይህን አሳሳቢ የሆነውን እና የትራፊክ አደጋ ዋነኛ መንስኤንም ከስሩ ለመንቀል ባለስልጣኑ ሀገራዊ ስርአት ልዘረጋ ነው ብሏል።

ስርአቱ በሁለት ምእራፍ የተከፈለ ሲሆን፥ ባለስልጣኑ በዚህ አመት ወደ ትግበራ የሚያስገባው እና የመጀመሪያው ስርአትም የመረጃ ቋት በማዘጋጀት በሀገሪቱ ሁሉም ክፍሎች ያሉ አሸከርካሪዎችን የመንጃ ፍቃድ መቆጣጠር የሚያስችል ነው።

የአሽከርካሪዎቹን የመንጃ ፍቃድ ወደ ቋት የማስገባት ስራ መጀመሩ የገለፁት አቶ ካሳሁን፥ በዚህ ስርአትም መንጃ ፈቃዱን የሚወስዱት ብቻ ሳይሆን የሚሰጡት አካላትም የሚካተቱ ይሆናል ብለዋል።

ሁለተኛው ስርአት ደግሞ ዘላቂ የሚሆን እና ለትራንስፖርት ዘርፉ ተብሎ ከአለም ባንክ ጋር የሚተገበረው ፕሮጀክት ነው።

ፕሮጀክቱ በቀጣዮቹ ሁለት አመታት ወደ ትግበራ የሚገባ ሲሆን፥ ይህ ወደ ትግበራ እስከሚገባ ድረስ ግን ባለስልጣኑ በዚህ አመት የሚጀምረው ስርአት ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል።

በአለም ባንክ የሚተገበረው ፕሮጀክትም “የትራንስፖርት ዘርፉን በመረጃ ስርአት የማገናኘት ፕሮጀክት” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፥ ከአለም ባንክ የተገኘ 300 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የብድር በጀት ተይዞለታል።

ከዚህ አጠቃላይ የትራንስፖርት ዘርፉን ለማስተሳሰር ከተያዘው የብድር በጀት ውስጥ ለአሽከርካሪ እና ተሽከርካሪ የመረጃ ስርአት የሚውለው 90 ሚሊየን ዶላሩ መሆኑን ነው የባለስልጣኑ መረጃ የሚያሳየው።

በዚህ በጀት የሚዘረጋው ስርአትም በሀገሪቱ ያሉ መረጃዎችን በአንድ መቆጣጠር የሚስችል እና አሽከርካሪው መንጃ ፍቃድ ለማውጣት ከተመዘገበበት አንስቶ ፍቃዱ እስከሚያገኝበት ድረስ ያሉ ሂደቶችን በየጊዜው የሚያሳይ እና የሚያሳውቅ ነው።

ስርአቱ ወደ ትግበራ ሲገባ የትኛውም ተቆጣጣሪ አካል በቀላሉ የሞባይል ኔትወርክን ተጠቅሞ መቆጣጠር የሚችልበት አሰራር ነው ተብሏል። እንዲሁም ህጋዊ ያልሆኑ መንጃ ፈቃዶችን በቀላሉ መለየት የሚያስችልም ነው።

የሚታተሙት መንጃ ፍቃድ ቁጥሮችንም የተለያዩ ማድረግ የሚችል አሰራር መሆኑን እና ችግሩንም ለመቅረፍ ትልቅ መፈትሄ መሆኑን ነው ዳይሬከተሩ የሚናገሩት።

በዙፋን ካሳሁን