የኢትዮ-ጂቡቲ የጋራ የድንበር ኮሚሽን ስብሰባ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 3 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) 24ኛው የኢትዮ - ጂቡቲ የጋራ የድንበር ኮሚሽን ስብሰባ በሰመራ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጎረቤት ሀገራትና ኢጋድ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር መሃመድ ድሪል፥ የኢትዮ-ጂቡቲ የሁለትዮሽ ግንኙነት በጋራ ጉዳዮቻቸው ዙሪያ ከመምከር ባለፈ የህዝብ ለህዝብ ትስስራቸውን የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።

መድረክ የሃገራቱን ህዝቦች ኑሮ ለማሻሻል የሚረዳ ጠቃሚ የሃሳብ ልውውጥ የሚደረግበት እንደሆነም ነው የተናገሩት።

የጋራ ድንበር ኮሚሽኑ ህገ ወጥ የሰዎችና የጦር መሳሪያ ዝውውር እንዲሁም የኮንትሮባንድ ንግድን በመከላከል ረገድ አበረታች ስራዎች አከናውኗል ብለዋል።

መድረኩ ሃገራቱ ስኬታቸውን ይበልጥ የሚያጎለብቱና የጋራ ችግሮቻቸውን በመለየት፥ የመፍትሄ አቅጣጫ እንደሚቀመጥበትም ገልጸዋል።

የጂቡቲ መንግስት ልዑክ ቡድን መሪ ሱሌይማን ኡመር አብዱልቃድር በበኩላቸው፥ ሃገራቱ ያላቸውን የቆየ ወዳጅነት በባህልና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ማጠናከራቸውን ጠቅሰዋል።

በኮሚሽኑ ስብሰባም በድንበር ንግድ፣ በሰዎችና እቃዎች እንቅስቃሴ ሂደት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ጠቃሚ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ አንስተዋል።

ኢትዮጵያና ጂቡቲ ግንኙነታቸውን በማጠናከር ወደ ኢኮኖሚያዊ ውህደት እየተሸጋገሩ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ።

የሁለቱ ሀገራት የጋራ ድንበር ኮሚሽን ስብሰባ እስከ መጋቢት 6 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ቀጥሎ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ እንደሚመክር ኢዜአ በዘገባው አስታውሷል።