የተመድ ዋና ፀሀፊ የኢትዮጵያ መንግስት የጀመራቸውን ማሻሻያዎች ድርጅታቸው እንደሚደግፍ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ትናንት ማምሻውን በቃል አቀባያቸው በኩል እንዳሉት፥ የተለያዩ እስረኞችን ከመልቀቅ ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግስት እያደረጋቸው ያለውን ማሻሻያዎች ተመድ ያደንቃል።

መንግስት እነዚህን ማሻሻያዎች እና የዜጎችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች እንዲቀጥልበትም ጉተሬዝ ጠይቀዋል።

ዋና ፀሃፊው በመግለጫቸው፥ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እና በመላው አህጉሪቱ በሰላም፣ በፀጥታ፣ በልማት፣ በረድኤት ስራ እና በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ተመድ ዋጋ የሚሰጣት አጋር መሆኗን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ለልማት እና መረጋጋት የሚያደርጉትን ጥረት ድርጅቱ እንደሚደግፍም በመግለጫቸው አረጋግጠዋል።