በአመት ለመንገድ ጥገና የሚወጣውን 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ ለመቀነስ ጥረት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 15 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በአመት ለመንገድ ጥገና የሚወጣውን 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ ለመቀነስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ፈንድ ጽህፈት ቤት አስታወቋል።

የአፍሪካ መንገዶች ፈንድ ማህበር የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎትን ዛሬ እየጎበኘ ነው።

ጉብኝቱ የአፍሪካ መንገዶች ፈንድ ማህበር በአዲስ አበባ እያካሄደ ካለው 16ኛ አመታዊ ጉባኤ ጎን ለጎን የሚካሄድ ነው።

በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ጎብኝዎችም ኢትዮጵያ በባቡር ትራንስፖርት ዘርፍ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኗን ጠቅሰው፥ የባቡር አገልግሎቱን አድንቀዋል።

ጉብኝቱ በሀገራቸው የተጀመሩ የመንገድ ስራዎችን ለማጠናቀቅና ያልተጀመሩትን ለማስጀመር ትልቅ መነሳሳትን እንደፈጠረላቸውም ተናግረዋል።

የአፍሪካ መንገዶች ጥገና ፈንድ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ረሺድ መሃመድ ጉብኝቱ የትራንስ አፍሪካ ሃይዌይ አካል የሆነውና ከዳካር ጅቡቲ እንዲሁም ከኬፕታዎን ካይሮ በሚዘረጋ መስመር የአፍሪካ ሃገራትን በትራንስፖርት ለማገናኘት የተያዘው እቅድ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የእቅዱ አካል የሆነውን በሃገሪቱ የተጀመረው የባቡር አገልግሎት፥ ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሃገራት ጋር በባቡር ትራንስፖርት ለማገናኘት እንቅስቃሴ መጀመሩን ማሳያ ነው ብለዋል።

አቶ ረሺድ አሁን ላይ ሃገሪቱ ለመንገድ ጥገና የምታወጣው ወጪና የምታገኘው ገቢ ተመጣጣኝ አለመሆኑንም በዚህ ወቅት ገልጸዋል።

ከዚህ አንጻርም ይህን ማስተካከል የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፥ ጥናቱ ሲጠናቀቅ የሚስተዋለውን ችግር እንደሚቀርፍ አንስተዋል።

አሁን ላይ ኢትዮጵያ ከሃገር ውስጥ ምንጭ በሚገኝ ገቢ በአመት 30 ሺህ ኪሎ ሜትር መንገድ የመጠገን ደረጃ ላይ የደረሰች ሲሆን ለዚህም 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ ታደርጋለች።

 

 


በቤተልሄም ጥጋቡ