በ2 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ወጪ ግንባታው የተጀመረው የኢትዮጵያ ናይል መስኖ ፕሮጀክት ዛሬም ድረስ አልተጠናቀቀም

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 7 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሁለት አመት በፊት ይጠናቀቃል የተባለውና በ2 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ወጪ ግንባታው የተጀመረው የኢትዮጵያ ናይል መስኖ ፕሮጀክት ዛሬም ድረስ አልተጠናቀቀም።

በውሀ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የሚሰራው ፕሮጀክት በውስጡ ሁለት ንዑስ ፕሮጀክቶች ሲኖሩት፥ ግንባታው ከአለም ባንክ በተገኝ ብድርና በፌደራል መንግስት በጀት በጥምረት የሚከናወን ነው።

የዚህ ፕሮጀክት አንዱ አካል የሆነው በሰሜን ጎንደር ዞን ጎርጎራ አካባቢ የሚገነባው የመገጭ ሰራባ ፓምፕ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ሲሆን ከጣና ሀይቅ ውሃ በመሳብ ጥቅም ላይ የሚውል ነው።

3 ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅምና 6 ሺህ አባወራዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ለተባለው ለዚህ ፕሮጀክት፥ 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ወጪ ይደረግበታል።

ግንባታው 2005 ዓ.ም ተጀምሮ በሶስት አመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ የታቀደው ይህ ፕሮጀክት ዛሬም ድረስ አልተጠናቀቀም።

የውሀ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴርም የዲዛይን ለውጥና የመሬት አቅርቦት ችግር ለፕሮጀክቱ መጓተት ምክንያት መሆናቸውን ይገልጻል።

የተቋራጩ እና የአማካሪ ድርጅቱ የሰው ሀይልና ማሽን አሟልቶ በበቂ ደረጃ በወቅቱ ወደስራ ያለመግባትም ለመዘግየቱ ሌላው ምክንያት መሆኑን፥ የተቋሙ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ ተናግረዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህን ቢልም የአማራ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቀቀም ቢሮ ግን ምክንያቱ ከእውነት የራቀ ነው ይላል።

የቢሮው ምክትል ሀላፊ አቶ መለሰ ዳምጤ እንደሚሉት በህጉ መሰረት መሬት ከአርሶ አደሩ ለማስለቀቀቅ ከ6 ወር እስከ 1 አመት ቀድሞ መጠየቅ ቢገባም ይህን ተከትሎ ባለመሰራቱ አርሶ አደሩ ላይ ቅሬታ እየተፈጠረ ነው ብለዋል።

አርሶ አደሩ ልማቱን ስለሚፈልገው መሬቱን ካለካሳ በመልቀቅ እንደተባበረና ካሳ ሳያገኝ እስከ 2 አመት መቆየቱንም አስረድተዋል።

ሌላው ንዑስ ፕሮጀክት በእብናት ወረዳ የርብ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት የሚገነባ ሲሆን 5 ሺህ 700 አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግና 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በጀት የተያዘለት ነው።

ዑስ ፕሮጀክቱ እስከ 13 ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ቢኖረውም፥ በመጀመሪያ ዙር 3 ሺህ ሄክታር ብቻ የሚያለማ መሆኑን አቶ ብዙነህ ይገልጻሉ።

አቶ ብዙነህ ይህ ንዑስ ፕሮጀክት አሁን ላይ አፈጻጸሙን 63 በመቶ በማድረስ ግንባታው አልዘገየም ቢሉም፥ የአማራ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቀቀም ቢሮ ግን ፕሮጀክቱ ዘግይቷል ባይ ነው።

የቢሮው ምክትል ሀላፊ አቶ መለስ ግንባታው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንዳለው በ2008 ሳይሆን በ2002 ዓ.ም እንደተጀመረ በማንሳት ከተባለው ጊዜ እጅግ መዘግየቱን ጠቅሰዋል።

መዘግየቱ እንዳለ ሆኖ ግን የውሀ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ፕሮጀክቱን በዚህ አመት ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ እየሰራሁ ነው ብሏል።

ፕሮጀክቱን የሚቆጣጠረው እና የሚከታተለው የፈረንሳይ ቢ አር ኤል የተሰኘው ኩባንያም ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ለአምስት አመት የሚያስተዳድረው ይሆናል።

ንዑስ ፕሮጀክቶቹ በተባለው ጊዜ ከተጠናቀቁ 50 ሺህ ሰዎችን በመስኖ ልማት ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

 

 

በቤተልሄም ጥጋቡ