እንቅስቃሴ ተስጓጉሎባቸው የነበሩ አንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው እየተመለሱ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል መንገድና የንግድ ተቋማት ተዘግተውባቸው የነበሩ ከተሞች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ መመለስ መጀመራቸውን የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ኡሚ አባጀማል በኦሮሚያ ክልል ተፈጥሮ የነበረውን የንግድ እንቅስቃሴ ማቆምና የመንገድ መዝጋት እንዲሁም የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፥ ባለፉት ሁለት ቀናት በክልሉ በሚገኙ ከተሞች የገበያ ማቆም እና መንገድ መዝጋት ሂደቶች እንደነበሩና ወደ ሁከት እና ብጥብጥ የመለወጥ አዝማሚያ ታይቶ እንደበረ አስታውሰዋል።

ተግባሩ በሰው ህይወትም በንብረትም ላይ ጉዳት ስለሚያደርስ በአፋጣኝ እንዲቆም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን እና ወጣቶችን በማወያየት ከተሞቹ ወደ መደበኛ አገልግሎት እንዲመለሱ መንግስት ጥሪ ማስተላለፉ ይታወሳል ነው ያሉት።

በዚህም መሰረት ከተወሰኑ አካባቢዎች ውጭ በዛሬው እለት አብዛኛው አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የንግድ ተቋማት ተከፍተው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ብለዋል ወይዘሮ ኡሚ።

ተዘግተው የነበሩ መንገዶችም ተመልሰው ለትራንስፖርት ክፍት መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው ከተመለሱ ከተሞች ውስጥም አዳማ፣ መቱ፣ ሻሸመኔ፣ አምቦ፣ ቢሾፍቱ እና ሌሎች ይገኙበታል ብለዋል።

ከተሞቹ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው እንዲመለሱ መንግስት ጥሪ ባስተላለፈው መሰረት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አባ ገዳዎች፣ የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በክልሉ መንግስት ስም ምስጋና አቅርበዋል።

በአሁኑ ወቅትም በነቀምቴ፣ ወሊሶ፣ ቡራዩ፣ ለገጣፎና ሆለታ ከተሞች፥ በተወሰነ ደረጃ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ አልገቡም ነው ያሉት።

ከተሞቹ ሙሉ በሙሉ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው እንዲመለሱ የመንግስት መዋቅር ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከከተሞቹ ነዋሪዎች እና የወጣት ተወካዮች ጋር ውይይት እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፥ ነገ ወደ መደበኛ ተግባራቸው ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።

ከሰኞ ጀምሮ በተደረገው የገበያ ማቆም እና የመንገድ መዝጋት ተግባር ወደ ሁከትና ብጥብጥ እንዲሁም ንብረት የማውደም አዝማሚያዎች መታየታቸውንም ጠቅሰዋል።

ወደ ሁከት እና ብጥብጥ በተቀየሩ ከተሞች ላይ በእርስ በእርስ ግጭት በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱንም ነው የገለጹት።

በዚህም መሰረት የ9 ሰዎች ህይወት አልፏል ያሉት ወርዘሮ ኡሚ፥ በምስራቅ ሸዋ 2፣ በሆለታ 1፣ በባቱ 1፣ በጅማ 3 እንዲሁም በሀረማያ 2 ሰዎች ህይዎታቸው ማለፉን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የፀጥታ ሀይሎችን ጨምሮ በ13 ሰዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው የመቁሰል አደጋ መድረሱን አንስተዋል።

የክልሉ መንግስት በዚህ ሁከትና ብጥብጥ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች ልባዊ ሀዘን እንደተሰማው ገልጸው፥ ህይዎቸውን ላጡ ዜጎች ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል።

መንግስት በሰው ህይወት መጥፋት በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ የተሳተፉ አካላትን በአስቸኳይ በማጣራት ለህግ የሚያቀርብ መሆኑንም ገልፀዋል።

የክልሉ መንግስት ከህዝቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን በቀጣይም ትኩረት ሰጥቶ ለመመለስ ይሰራል ያሉት ወይዘሮ ኡሚ፥ ቃል በተገባው መሰረት የታሰሩ ሰዎች እየተፈቱ ነው፤ ይህም ቀጣይነት ይኖረዋል ነው ያሉት በመግለጫቸው።

በቀጣይ መንግስት በሚሰራቸው ስራዎች ላይም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እና ወጣቱ ከመንግስት ጎን በመቆም እንዲተባበር ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።