ከፀሀይ 100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሀይል በግል ባለሀብት ማመንጨት ሊጀመር ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከፀሀይ 100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሀይል በግል ባለሀብት ለመጀመሪያ ጊዜ ማመንጨት ሊጀመር ነው።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘርፉን ከሚመራው የውሀ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚንስቴር የሀይል ማመንጨት ስራው ሊጀመር መሆኑን መረጃውን ሰምቷል።

በሚንስቴር መስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ብዙነህ ቶልቻ፥ የጨረታ ሂደቱ ተጠናቆ ሀይሉን የሚያመነጨው የግል ባለሀብት መለየቱንና የመጨረሻውን የስምምነት ፊርማ ለማኖር በሂደት ላይ መሆናቸውን ነግረውናል።

በሀገር ውስጥ የግል ባለሀብት በቅርቡ ይመነጫል ተብሎ የሚጠበቀው የኤሌክትሪክ ሀይል ተግባራዊ የሚሆነው በመትሀራ አካባቢ ነው።

የግል ባለሀብቱ ዘርፉን ከሚመራው የውሀ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚንስቴር ጋር የመጨረሻ የስምምነት ምእራፉን ካጠናቀቀ በኋላ የሚያመነጨውን ሀይል ለመንግስት ይሸጣል።

ይህንን ተግባር ለ20 ዓመታት በተከታታይ ካከናወነ በኋላ ለመንግስት የሚያስረክብ ሲሆን፥ ይህም የስምምነቱ አንዱ አካል መሆኑን ነው አቶ ብዙነህ ቶልቻ የተናገሩት።

ከውሀ ፤ ከንፋስና ከፀሀይ በግል ባለሀብቶች የኤሌክትሪክ ሀይል ለማመንጨት የሚያስችል ምቹ ፖሊሲና ስትራቴጂ መቀረጹንም አቶ ብዙነህ ቶልቻ ይናገራሉ።

የውጭ ሀገርና የሀገር ውስጥ የግል ባለሀብቶችና ኩባንያዎች በዘርፉ በስፋት እንዲሳተፉ የተለያዩ ማበረታቻዎች እየተደረጉ እንደሆነም ሰምተናል።

ከፀሀይ በተጨማሪ በጂኦ ተርማል የሀይል ማመንጫ ዘርፉ የግል ባለሀብቶች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ከሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ኮርቤቲ እና ቱሉ ሞዬ ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎች ከካናዳ ለመጡ ሁለት የግል ኩባንያዎች ጋር የስምምነት ውል ተፈርሞ የቦታ ርከክብ ተፈጽሟል።

በእነዚህ ሁለት አካባቢዎች የሀይል ማመንጫ ግንባታቸው ከተጠናቀቀ በኋላ እያንዳንዳቸው 500 ሜጋ ዋት ያመነጫሉም ተብሎ ይጠበቃል።

ግንባታውም ከ7 እስከ 8 ዓመት ድረስ ይፈጃልም ነው ያሉት አቶ ብዙነህ።

ሀገሪቱ ከ2 ዓመታት በኋላ በሚጠናቀቀው የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመን ከውሀ ከንፋስና ከጸሀይ 17 ሺህ 347 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሀይል ለማመንጨት በእንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች።

ከዚህ ወስጥ 4 ሺህ 284 ሜጋ ዋት ሀይል እስካሁን የመነጨ ሲሆን 9 ሺህ ሜጋዋት ሀይል ለማመንጨት የሚያስችሉ ግንባታዎችም በመካሄድ ላይ ናቸው።

በሰለሞን ጥበበስላሴ