የአሜሪካው ፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድና የእሲያ አጋሩ በኢትዮጵያ በ4 ቢሊየን ዶላር የነዳጅ ማጣሪያ ሊገነቡ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሜሪካው ፌርፋክስና ከእሲያ አጋሩ ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የነዳጅ ማጣሪያ ሊገነባ መሆኑ ተጠቆመ።

በ4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ግንባታው የሚካሄደው ፕሮጀክቱ ለኢትዮጵያ እና ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ገበያ የሚያገለግል መሆኑም ተነግሯል።

ከአዲስ አበባ በስተምስራቅ 220 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በትምተገኘው አዋሽ ከተማ የሚገነባው ማጣሪያው በቀን 120 ሺህ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ የማጣራት አቅም አለው።

ይህም ከ6 ሚሊየን ሜትሪክ ድፍድፍ ነዳጅ ጋር እኩል መጠን ያለው ነው።

ፌርፋክስ የአፍሪካ ፈንድ ዓለም አቀፍ ሊቀመንበር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ፥ በኢትዮጵያ በቀጣይ 10 እና 15 ዓመታት ውስጥ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ሽግግር ይደረጋል ብለዋል።

በዚህ ጊዜም በሀገሪቱ ያለው የትራንስፖርት ፍላጎት በከፍተኛ መጠን ይጨምራል፤ ለዚህ ሲባል ነው የነዳጅ ማጣሪያውን እዚህ ለመገንባት የታሰበው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚገነባው ማጣሪያው ስራው ነዳጅ ማጣራት ብቻ አይደለም፤ ነዳጅ ማጣራት የመጀመሪያው ስራው ቢሆንም በቀጣይ 15 ዓመታት ውስጥ ሙሉ “የፔትሮኬሚካል” ምርቶችን ማቅረብ ይጀምራልም ብለዋል አቶ ዘመዴነህ።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ዓመታዊ የነዳጅ ፍጆታ 3 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ነው።

አቶ ዘመዴነህ፥ “የነዳጅ ማጣሪያው ዋና ዓላማ ሁሉንም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ማገልገል ነው፤ በሚሊየን የሚቆጠሩ ህዝቦችን የያዙት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በአሁኑ ወቅት አንድ አነስተኛ የነዳጅ ማጣሪያ ብቻ ነው ያለው፤ ሆኖም ግን የቀጠናው ሀገራት በፍጥነት በማድግ ላይ ያሉ ናቸው” ብለዋል።

ወደፊት በምስራቅ አፍሪካ ከተሜነት በፍጥነት እየተስፋፋ ስለሚመጣ፤ ለዚህ ነው ይህን ፕሮጀክት ለመገንባት ያቀድነው ሲሉም ተናግረዋል።

“ለፕሮጀክቱ የተያዘው 4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ግምት ነው፤ የገንዘቡ መጠን እንደ አስፈላጊነቱ ሊቀንስ አሊያም ሊጨምር ይችላል” ብለዋል አቶ ዘመዴነህ።


ምንጭ፦ CGTN