የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ በሙስና ሊከሰሱ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሙስና መንጀል ክስ ሊመሰረትባቸው እንደሚችል የእስራኤል ፖሊስ አስታወቀ።

እንደ ፖሊስ ገለጻ በጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ላይ በጉቦ መቀበል፣ በማጭበርበር እና በእምነት ማጉደል የተለያዩ ክሶችን ለመመስረት የሚያስችል ሙሉ ማስረጃ አለ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ለእስራኤል ቴሌቪዥን ቀርበው በሰጡት መግለጫ፥ እየቀረበባቸው ያለው ውንጀላ መሰረተቢስ በማለት ያጣጣሉ ሲሆን፥ በጠቅላይ ሚኒስተርነት ስራቸው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

አሁን እየቀረበ ያለው ውንጀላም ያለ ምንም ውጤት የሚጠናቀቅ መሆኑን ገልፀዋል።

ከሙስና ወንጀል ጋር ተያይዞ ስማቸው እየተነሳ የሚገኘው ጠቅላይ ሚኒስተሩ፥ የእስራኤሉ ጋዜጣ የዶይት አህሮኖት በእሳቸው ላይ የሚወጡትን የውንጀላ ዘገባዎችን ውድቅ ለማድረግ ስለ እሳቸው በጎ ነገር እንዲፅፍ መጠየቃቸውም ተነግሯል።

ፖሊስ በበኩሉ የየዶይት አህሮኖት ጋዜጣ አርታኢ አሮን ሞዜስም ይህን ተግባር ከፈፀመ ክስ ይመሰረትበታል ነው ያለው።

በአሁኑ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ላይ እየቀሩ ካሉ ውንጀላዎች ውስጥ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2009 ጀምሮ አስራኤልን ሲመሩ ከሆሊውዱ አሮን ኪልቻን የ283 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የእጅ መንሻ ተቀብለዋል የሚል ነው።

ጄሩሳሌም ፖስት እንደዘገበው እጅ መንሻው ከገንዘብ በተጨማሪም ሻምፓኝ መጠጥ እና ውድ ሲጋራዎችን ያከተተ ነው።

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እጅ መንሻ የተሰጠውም የሆሊውድ ፊልም ፕሮዲውሰር አሮን ኪልቻን የአሜሪካ ቪዛ እንዲያገኙ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ነው ተብሏል።

አሮን ኪልቻን በአሁኑ ወቅት በአሜሪካው ሆሊውድ ውስጥ የፊልም ፕሮዲውሰር ሲሆኑ፥ ፕሮዲውስ ካደረጓቸው ፊልሞች ውስጥም “ፍላይት ክለብ፣ ጎን ገርል እና ዘ ሬቭናንት” ይገኙበታል።

የፊልም ፕሮዲውሰሩ አሮን ኪልቻን የሙስና ክስ ሊመሰረትባቸው እንደሚችል የእስራኤል ፖሊስ አስታውቋል።

ምንጭ፦ www.bbc.com