በቀጣዮቹ 10 ቀናት ውስጥ የበልግ ዝናብ መጣል ይጀምራል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቀጣዮቹ 10 ቀናት ውስጥ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የበልግ ዝናብ መዝነብ እንደሚጀምር የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጅ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ የሀገሪቱ ደቡብ ምዕራብ፣ የመካከለኛው፣ የሰሜን ምስራቅና የምስራቅ ክፍሎች ዝናብ ማግኘት ይጀምራሉ።

ባለፉት 10 ቀናት የአየር ጠባይ ሁኔታ የነበረው ገጽታ ሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎችና ተፋሰሶች ደረቃማና ከፊል ደረቃማ ሆነው መሰንበታቸውን ያስታወሰው መግለጫው፤ በቀጣይ ተመሳሳይ 10 ቀናት ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ጠቁሟል።

በዚህ መሰረት በኦሮሚያ ክልል ጅማ፣ ኢሉባቦር፣ ምዕራብና ሰሜን ሸዋ፣ ጥቂት የምዕራብና የምስራቅ ሃረርጌ፣ በአማራ ክልል ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ እንዲሁም በአዲስ አበባ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በተመሳሳይ በትግራይ ክልል የምስራቅና የደቡብ ትግራይ ዞኖች እንዲሁም በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ደግሞ የከፋ፣ የቤንች ማጂና የወላይታ ዞኖች አንዳንድ ቦታዎች ዝናብ ያገኛሉ ተብሎ ከሚጠበቁ አካባቢዎች መካከል ይገኙበታል።

ሌሎች የተቀሩት የአገሪቱ አካባቢዎች በአመዛኙ ደረቃማ የአየር ጸባይ እንደሚኖራቸውም ተጠቁሟል።

በቀጣዮቹ 10 ቀናት በአመዛኙ ከሚስተዋለው እርጥበታማ የአየር ሁኔታ ጋር ተያይዞ አብዛኛው የበልግ አብቃይ አካባቢዎች የማሳ ዝግጅት ተግባራት በስፋት የሚከናወንበት መሆኑን በመግለጫው ተጠቅሷል።

የዝናቡ መጣል ሰብሎች ሙሉ በሙሉ በተሰበሰቡባቸውና የበልግ ወቅት ዝግጅትን በሚያከናውኑ አካባቢዎች የአፈር እርጥበት ለማሻሻል በጎ ሚና ይኖረዋል ተብሏል።

ዝናቡ የድህረ ሰብል ስብሰባው ሙሉ በሙሉ ባልተጠናቀቀባቸው አካባቢዎች ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል አርሶ አደሩ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ አሳስቧል።

እንዲሁም አዋሽ፣ የላይኛው ተከዜ፣ የላይኛውና መካከለኛው ኦሞ፣ ጊቤና ስምጥ ሸለቆ፣ የላይኛው ገናሌ ዳዋ ተፋሰሶች በተወሰነ መልኩ እርጥበት የሚያገኙ ሲሆን፥ የተቀሩት የአገሪቱ ተፋሰሶች ግን ደረቃማ ሆነው ይቆያሉ ብሏል።

ምንጭ፦ ኢዜአ