የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ሃይሎች የፀጥታ ሃላፊ መሪዎች በአዲስ አበባ ይወያያሉ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 5 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ሃይሎች የፀጥታ ሃላፊ መሪዎች በነገው እለት በአዲስ አበባ እንደሚወያዩ ይጠበቃል። 

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ፥ የደቡብ ሱዳን የፀጥታ ሃይላት አደረጃጀትና ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነትን የያዘ ረቂቅ ሰነድ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ሚኒስትር ዲኤታዋ በነገው እለትም የሃገሪቱ ተፋላሚ ሃይላት የመከላከያ ሃይል ተወካዮች በሰነዱ ላይ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት።

ባለፈው አመት መጀመሪያ ላይ የመጀመሪያው ምዕራፍ የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት መተግበሪያ ማሳለጫ ድርድር ተካሂዶ ነበር።

በድርድሩም የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ፣ ሁለተኛው ምዕራፍ የሰላም ስምምነት መተግበሪያ ማሳለጫ ድርደር በአዲስ አበባ እንዲካሄድና አዲስ የፀጥታ አደረጃጀት ማዋቀር በሚቻልበት አግባብ ላይ ተወያይተዋል።

የሃገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች፣ የሲቪክ፣ የወጣቶችና የሴቶች ማህበራት እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎች አዲስ አበባ ውስጥ የሰላም ውይይት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

እስካሁንም ውይይቱ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑንም ወይዘሮ ሂሩት ተናግረዋል።

ተፋላሚ ሃይሎቹ በስልጣን ክፍፍልና የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ተወያይተዋልም ነው ያሉት።

የኢጋድ የደቡብ ሱዳን ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር እስማኤል ዋይስ በበኩላቸው፥ ኢጋድ ሁሉም ተፋላሚ ሃይላት ከዚህ ውይይት በኋላ ወሳኝ መፍትሄዎችን እንደዲያስቀምጡ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል።

 


በስላባት ማናዬ