እስራኤል በሶሪያ ድንበር አቅራቢያ ፀረ ሚሳኤል መሳሪያ ተከለች

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 5 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራኤል በሶሪያ ድንበር አቅራቢያ ፀረ ሚሳኤል መሳሪያ ተከለች።

ፀረ ሚሳኤል መሳሪያዎቹ በትናንትናው እለት ሃገሪቱ ከሶሪያ በሚዋስናት ድንበር አቅራቢያ መትከሏን የሃገሪቱን ጋዜጣ ጀሩሳሌም ፖስትን የጠቀሱ ዘገባዎች ያመላክታሉ።

ከተተከሉት ሚሳኤሎች ባለፈም በርካታ ፀረ ሚሳኤል መሳሪያዎችን የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ወደ ስፍራው መንቀሳቀሳቸውን የአይን እማኞች ተናግረዋል።

ባለፈው ቅዳሜ ከሶሪያ በተወነጨፈ ሚሳኤል አንድ የእስራኤል ተዋጊ አውሮፕላን ተመቶ ወድቋል።

ከዚህ ባለፈም እስራኤል በጎላን ኮረብታዎች አካባቢ ኢራን ሰራሽ የሆነ ሰው አልባ አነስተኛ አውሮፕላን ማግኘቷን ገልጻ ነበር።

ይህን ተከትሎም በሃገራቱ መካከል ያለው ፍጥጫ እየተጠናከረ ሲሆን፥ እስራኤልም በአካባቢው ለየት ያለ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እያደረገች ነው ተብሏል።

እስራኤልም ባለፈው ቅዳሜ ለተመታባት ተዋጊ አውሮፕላን አፀፋዊ ምላሽ እየሰጠች ነው።

እስካሁንም በደቡባዊ ሶሪያ በሚገኝ አውሮፕላን ማረፊያና ከመዲናዊ ደማስቆ አቅራቢያ በሚገኝ የጦር መሳሪያ መጋዘን ላይ ጥቃት ፈጽማለች ነው የተባለው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ኢራን በሶሪያ ምድር የምታደርገውን እንቅስቃሴና መስፋፋት እንድታቆም አስጠንቅቀዋል።

ሶሪያም ኢራን በሃገሯ ለምታደርገው መስፋፋት የምታደርገውን ድጋፍ እንድታቆም ሲጠይቁም ቆይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃገራቱ ከድርጊታቸው የማይታቀቡ ከሆነ ከባድ ዋጋ እንደሚከፍሉም ተናግረዋል።

ሩሲያ በበኩሏ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ያለውን ሁኔታ በአጽንኦት እየተከታተለችው መሆኑን ገልጻለች።

አሁን ላይ እስራኤል የምትከተለው አካሄድ አግባብ ያልሆነና በአካባቢው ያለውን ፍጥጫ የሚያባብስ ነው ብላለች።

 

ምንጭ፦ ፕረስ ቲቪ እና አልጀዚራ