የአፋር ክልል ምክር ቤት ከ140 ሚሊየን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት አጸደቀ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 4 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፋር ብሄራዊ ክልል ምክር ቤት ከ140 ሚሊየን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት አጸደቀ ፡፡

ምክር ቤቱ ሲያካሂድ የቆየውን 3ኛ አመት የስራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ጉባኤውን አጠናቋል።

በጉባኤው ላይ የ2010 በጀት አመት የስድስት ወር እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና የአስፈጻሚ አካላት የማሻሻያ ረቂቅ
አዋጅ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።

ምክር ቤቱ ብልሹ አሰራርና የስነ ምግባር ጉድለት የታየባቸው ስድስት ዳኞች እንዲሰናበቱ የቀረበለትን ሃሳብም አጽድቆታል።

በክልሉ በበጀት አመቱ ስድስት ወራት በ19 ወረዳዎች የመስኖ ውሀ በመጠቀም 2 ሺህ 228 ቶን የእንስሳት መኖ መመረቱም ተገልጿል።

ከዚህ ባለፈም በበጀት አመቱ ለመሰብሰብ ከታቀደው 790 ሚሊየን ብር ውስጥ በበጀት አመቱ አጋማሽ ከ348 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰብ ተችሏል።

በመንደር ማሰባሰብ ስራም በስድስት ወራት ውስጥ ከ3 ሺህ በላይ እማዋራና አባዋራዎችን ማሰባሰብ መቻሉ በጉባኤው ተጠቅሷል።

በክልሉ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝም ለ8 ሺህ 279 ወጣቶች የስራ ዕድል መፈጠሩን የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።