ከ200 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የወላይታ ሶዶ የንጹህ መጠጥ ውሀ ፕሮጀክት ተመረቀ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 13 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ200 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የወላይታ ሶዶ ከተማ ዘላቂ የንጹህ መጠጥ ውሀ እና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ዛሬ በይፋ ተመርቋል።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፥ ፕሮጀክቱ የከተማዋን 158 ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

በተለምዶ ሊቂምሴ በመባል የሚታወቀው ይህ ፕሮጀክት ግንባታው በተለያየ ምክንያት ቢዘገይም፥ የከተማዋን ማህበረሰብ የረጅም ጊዜ ጥያቄ የሚፈታ መሆኑንም ነው ሚኒስትሩ ያነሱት።

ዛሬ ከተመረቀው የውሃ ፕሮጀክት ጋር በአራት ክልሎች የተጀመሩ 13 ፕሮጀክቶችም ተጠናቀው አገልግሎት መጀመራቸውንም ተናግረዋል።

መሰል ፕሮጀክቶችን ከማልማት ባለፈ የተገነቡትን መጠበቅ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የንፁህ መጠጥ ውሃ መሰረተ ልማቶችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የተፋሰስ እና ተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ስራ ዋነኛ አማራጭ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባውም ገልጸዋል።

መረጃውን የወላይታ ሶዶ ፋና ኤፍ ኤም ባልደረባችን ተመስገን ተስፋዬ አድርሶናል።