ጀርመን በየመን ቀውስ ተሳታፊ ለሆኑ ሃገራት የመሳሪያ ሽያጭ ልታቆም እንደምትችል አስታወቀች

አዲስ አበባ ፣ ጥር 13 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ጀርመን በየመን ቀውስ ተሳታፊ ለሆኑ ሃገራት የምታደርገውን የመሳሪያ ሽያጭ ልታቆም እንደምትችል አስታወቀች።

የአንጌላ ሜርክል ቃል አቀባይ በርሊን በየመን ቀውስ ውስጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተሳታፊ ለሆኑ ሃገራት የምታደርገውን የመሳሪያ ሽያጭ ልታቆም ትችላለች ብለዋል።

ቃል አቀባዩ አሁን ላይ ሃገራቸው ወደ እርምጃ እንደማትገባ ጠቅሰው፥ እየተደረገ ካለው የጥምር መንግስት ምስረታ ድርድር በኋላ ጉዳዩ እንደሚታይ ገልጸዋል።

ጀርመን ውሳኔውን ተግባራዊ የምታደርግ ከሆነ ለሳዑዲ ዓረቢያ ከምትሸጠው መሳሪያ ከፍተኛ ገንዘብ ልታጣ ትችላለች ተብሏል።

የሃገሪቱ ሚዲያዎችን ዋቢ ያደረጉ ዘገባዎች በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2017 ሶስተኛ ሩብ አመት፥ ጀርመን ለሪያድ የሸጠችው መሳሪያ ዋጋ 550 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር መድረሱን ያሳያሉ።

ከፈረንጆቹ 2015 ጀምሮ በየመን ቀውስ ውስጥ ያለችው ሳዑዲ ዓረቢያ በሃውቲ አማጽያን ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ስትፈጸም ቆይታለች።

የአሁኑ የጀርመን መግለጫም በዋናነት ሳዑዲን ሳይመለከት አይቀርም ነው የተባለው።

መግለጫውን ተከትሎም በርካታ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም የጀርመንን ሃሳብ አድንቀዋል።

እንደ አሜሪካ፣ ብሪታንያና ፈረንሳይ ያሉ ሃገራትም የጀርመንን አካሄድ እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በርካታ ምዕራባውያን ሃገራት በየመን ግጭት ውስጥ ተሳታፊ ለሆኑ ሃገራት በርካታ መጠን ያለው የመሳሪያ ሽያጭ እንደሚያደርጉ ይነገራል።

ብሪታንያ የየመን ቀውስ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን 6 ነጥብ 3 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ያለው የመሳሪያ ግዥ ስምምነት ከሳዑዲ ጋር መፈጸሟን መረጃዎች ያመላክታሉ።

እልባት ያጣው የየመን ቀውስ ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑት ህልፈትና ከ2 ሚሊየን ለሚበልጡት ደግሞ መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።

 


ምንጭ፦ አልጀዚራ