ቱርክ በሰሜናዊ ሶሪያ በሚንቀሳቀሱት የኩርድ ታጣቂዎች ላይ ጥቃት መፈጸም ጀመረች

አዲስ አበባ ፣ ጥር 11 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ቱርክ በሰሜናዊ ሶሪያ በሚንቀሳቀሱት የሶሪያ የኩርድ ታጣቂዎች ላይ መጠነ ሰፊ እርምጃ መውሰድ ጀምራለች።

ከትናንት ጀምሮ አፍሪን በተባለችው የሶሪያ አካባቢ በሚገኙ የኩርድ ታጣቂዎች ላይ ወታደራዊ እርምጃ እየወሰደች ትገኛለች።

አንካራ ከፈረንጆቹ 2012 ጀምሮ በኩርድ ታጣቂዎች ይዞታ ስር የሚገኘውን ስፍራ ለማስለቀቅ አሁን ላይ የተጠናከረ ዘመቻ መጀመሯም ነው የተነገረው።

የሃገሪቱ ወታደራዊ ባለስልጣናትም በአፍሪን የአየር ክልል ላይ የአየር ላይ ጥቃት መፈጸም የሚችሉበትን ይሁንታ ለማግኘት ሩሲያ ናቸው ተብሏል።

ቱርክ የኩርድ ታጣቂዎችን ከኩርድ የሰራተኞች ፓርቲ (ፒኬኬ) ጋር ግንኙነት አለው በሚል ከአካባቢው ለማስወገድ እየተንቀሳቀሰች ነው።

የሃገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ኑረቲን ካኒክሊ አንካራ ለደህንነቷ ስጋት በሆኑ ሃይሎች የተጠናከረ እርምጃ እንደምትወስድ ገልጸዋል።

የኩርድ ታጣቂዎች በበኩላቸው ምሽቱን ከቱርክ ጦር 70 የከባድ መሳሪያ አረሮች እንደተተኮሱባቸው ተናግረዋል።

የቱርክን እርምጃ ተከትሎም ሩሲያ ወታደሮቿንና ወታደራዊ ታዛቢዎችን ከስፍራው ማስወጣት ጀምራለች ነው የተባለው።

የአሁኑን ወታደራዊ እርምጃም ሞስኮ ትቃወማለች ብለው እንደማይጠብቁ አንድ የቱርክ ፓርላማ አባል ተናግረዋል።

 


ምንጭ፦ ቢቢሲና አልጀዚራ