ቻይና በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ አመት የ6 ነጥብ 9 በመቶ እድገት አስመዘገበች

አዲስ አበባ ፣ ጥር 10 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይና ኢኮኖሚ በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ አመት በ6 ነጥብ 9 በመቶ ማደጉ ተገለጸ።

ኢኮኖሚያዊ እድገቱ የቻይና መንግስት አስመዘግበዋለሁ ብሎ ካስቀመጠው እቅድ በ0 ነጥብ 4 በመቶ ከፍ ያለ ነው ተብሏል።

አሁን ቻይና ያስመዘገበችው እድገት በሁለት አመታት ውስጥ ትልቁ ሲሆን፥ ከቀደመው አመት አንጻር ብልጫ በማሳየት ደግሞ በሰባት አመታት ውስጥ የመጀመሪያው ሆኖ ተመዝግቧል ነው የተባለው።

ይህ መሆኑም መዋዕለ ንዋያቸውን በቻይና ማፍሰስ ለሚፈልጉ ባለሃብቶች የምስራች መሆኑ እየተነገረ ነው።

ተንታኞች ግን የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ቢያድግም አጠቃላይ የሃገር ውስጥ ምርት እድገቱ ከተጠበቀው በታች ይሆናል እያሉ ነው።

ከአመታዊው ኢኮኖሚያዊ እድገት ባለፈም ቻይና በፈረንጆቹ 2017 የመጨረሻ ሶስት ወራት በተከታታይ 6 ነጥብ 8 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት ማስመዝገቧም ተገልጿል።

ይህ አሃዝ ባለሙያዎች ይመዘገባል ብለው ከተነበዩት አንጻር ከፍተኛው ሆኗል።

ሃገሪቱ ይህን መሰል ኢኮኖሚያዊ እድገት ብታስመዘግብም የመንግስት የብድር መጠን ግን ከፍተኛ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።

አሁን ላይ የሃገሪቱ መንግስት ከሃገር ውስጥ አበዳሪ ተቋማትና ባንኮች የወሰደው የብድር መጠን ከፍ እያለ መሆኑንም ነው መረጃዎች የሚያሳዩት።

አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋምም መንግስት የሃገሪቱን ባንኮች የፋይናንስ አቅም ማጠናከርና መሰል ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደሚገባው አሳስቧል።

ከዚህ ባለፈም ቻይና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር በሚል ያወጣቻቸው ድንጋጌዎች የሃገሪቱን ኢኮኖሚ እየጎዳው ነው በሚልም ታዛቢዎች ይናገራሉ።

ድንጋጌዎቹ ከፍተኛ የበካይ ጋዝ የልቀት መጠን ያላቸው ፋብሪካዎች የምርት መጠናቸውን በማሳነስ ወደ ከባቢ አየር የሚለቁትን የበካይ ጋዝ መጠን መቀነስን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው።

ይህ መሆኑ ደግሞ በተለይም በሲሚንቶና ብረት አምራች ፋብሪካዎች የምርት መጠን ላይ ከፍተኛ ልዩነት በመፍጠር በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ማስከተሉን ነው ባለሙያዎቹ የሚናገሩት።

ግዙፍ ፋብሪካዎችን ምርት መቀነስ ወይም ማቋረጥን በተመለከተ በ28 ግዙፍ ከተሞቿ ላይ ያሳለፈችው ውሳኔ በቤት ውስጥም ተግባራዊ ይደረጋል።

ይህም ነዋሪዎቹ ከፍተኛ በካይ ጋዝ አማቂ ከሆኑ ምርቶች ይልቅ የአረንጓዴ ኢኮኖሚን በሚያበረታታ መልኩ የቤት ፍጆታቸውን እንዲሸፍኑ የሚያደርግ ነው።

 

 


ምንጭ፦ ቢቢሲ