በትግራይ 125 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ግንባታ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል 125 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ግንባታ ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።

የባልስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶም ወንድሙ እንደገለጹት፥ ለመንገዱ ግንባታ ከፌዴራል መንግስት 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በጀት ተመድቧል።

የሚገነባው መንገድ በትግራይ ማዕከላዊ እና ምስራቃዊ ዞኖች "ከውቅሮ- አብረሃ ወአፅበሃ - ነበለት- ማይቅነጣል" ከተሞች እና ወረዳዎችን የሚያገናኝ ነው ።

የመንገዱ ግንባታ ሥራ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃል ብለዋል።

የመንገዱ ግንባታ በጥራት እና በፍጥነት እንዲጠናቀቅ የክልሉ መንግስት ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም አቶ ሳምሶም አስታውቀዋል።

በትግራይ ማዕከላዊ ዞን የወርዒ ለኸ ወረዳ የኮንስትራክሽን፣ መንገድ እና ትራንስፖርት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግደይ ተኽሉ በበኩላቸው፥ የመንገዱ ግንባታ ይጀመራል ከተባለው ጊዜ የዘገየ በመሆኑ ሥራው ፈጥኖ እንዲጀመር ጠይቀዋል።

መንገዱን የሚሰራው ሱር ኮንስትራክሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ የማነ፥ ድርጅታቸው መንገዱን ለመገንባት ከፌዴራል መንግስት ጋር ጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም መፈራረሙን ገልጸዋል።

በተፈራረመው የውል ስምምነት መሰረት በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ሥራውን በጥራት አጠናቆ ለማስረከብ ዝግጅት መደረጉንም አመልክተዋል።

እንደ አቶ ታደሰ ገለፃ በአሁን ወቅት ከባድ ማሽነሪዎችን ወደ ቦታው የማስገባት ሥራ እያከናወኑ ይገኛሉ።

 

 

 

ምንጭ፥ ኢዜአ