እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2010(ኤፍ.ቢ.ሲ) ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ከፍተኛ የፌደራል እና የክልል የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተመረቀ።

በክብር እንግድነት ተገኝተው ዩኒቨርሲቲውን ዛሬ የመረቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደተናገሩት፥ መንግስት በሀገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ለማስፋፋት ከፍተኛ በጀት መድቦ እየሰራ ነው።

በሀገሪቱ በቅርቡ ተመርቀው ወደ ስራ ከገቡ አዳዲስ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ በሚያከናውነው የመማር ማስተማር ሥራ በአካባቢው ለተጀመረው የልማት እንቅስቃሴ ትልቅ አቅም እንደሚሆንም ተናግረዋል።

የፌደራል መንግስት ከክልሉ መንግስት ጋር በመተባበርና ከፍተኛ በጀት በመመደብ ዩኒቨርሲቲው እንዲገነባ ማድረጉን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፥ ተቋሙ በእውቀት የበቁና ሀገራቸውን በልማት ወደፊት የሚያራምዱ ዜጎችን ለማፍራት አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።

88b35d05afc51657eca756bf956e09c1_XL.jpg

የአካባቢው ሕብረተሰብ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ወደዩኒቨርሲቲው የመጡ ተማሪዎችን እንደራሱ ልጆች ከመንከባከብ ባለፈ ትምህርታቸውን ተረጋግተው እንዲማሩ የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

በምረቃ ሥነስርአቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ዛሬ ከቀትር በኋላ ከእንጅባራ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ጋር ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

ምንጭ፦ ኢዜአ