አገልግሎት እንዳይሰጥ የተወሰነበት ፀረ-ተባይ ዲዲቲ ከኢትዮጵያም ሊወገድ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆን የተወሰነበትን ፀረ-ተባይ ዲዲቲ ከኢትዮጵያ ለማስወገድ እንቅስቃሴ መጀመሩን የአካባቢ ደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ መረጃ እንደሚያመለክተው ዲዲቲ የተሰኘው ጸረ-ተባይ ኬሚካል ከ1930ዎቹ ጀምሮ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን፥ ከ1960ዎቹ ወዲህ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ በመታወቁ እና ሀገሮችም በሂደት መግባባት ላይ በመድረሳቸው በስቶኮልም ስምምነት ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆን ተወስኗል።

ይኸው ዲዲቲ በኢትዮጵያ የወባ ትንኝን ለመከላከል አገልግሎት ላይ ይውል እንደነበር ይታወቃል።

ስምምነቱን የፈረመችው ኢትዮጵያም በዲዲቲ ምትክ ወባን በተሻለ የሚከላከል "ኢንዶ ሰልፋን" የተሰኘ ኬሚካል አገልግሎት ላይ በማዋል ከ1 ሺህ 400 ሜትሪክ ቶን በላይ ዲዲቲ ለማስወገድ እየሰራች ነው።

የሚኒስቴሩ የህግ ማስከበር ክትትል እና ቁጥጥር ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ መሃሪ ወንድምአገኝ እንደገለጹት፥ በስቶኮልሙ ስምምነት መሰረት የዲዲቲ ኬሚካልን ከአገሪቱ የማስወገዱ ተግባር ተጀምሯል።

የዲዲቲ ክምችቱን ለማስወገድ የቆጠራ፣ ስልጠና የመስጠት፣ ኬሚካሉን ሊያመክን የሚችል መሳሪያ አገር ውስጥ ባለመኖሩም ከአውሮፓ እና ከሌሎች አገሮች ጋር ስምምነት የማካሄድ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

በሀገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ተከማችቶ የሚገኘውን ዲዲቲ ለማስወገድ የሁለት ዓመት ጊዜ እንደሚወስድም አቶ መሃሪ ተናግረዋል።

ኬሚካሉን አስወግዶ ለመጨረስ 3 ሚሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ዳይሬክተሩ ዲዲቲ በኢትዮጵያ መመረት ካቆመ ከሰባት ዓመት በላይ እንደሆነው አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር 2011 ኬሚካሉን ማምረት የቆመ በመሆኑ በዚህ ሂደት የተከማቸ እንጂ ጥቅም ላይ ሳይውል የቀረ አለመሆኑንም ነው የገለጹት።

ኬሚካሉ ሳይመክን በአየር ላይ ለረጅም ጊዜ የመቆየትና ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ባህሪ ያለውና በሰዎች ጤና ላይ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ በጥንቃቄ መቀመጡንም ገልጸዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በአዳሚ ቱሉ ፀረ-ተባይ ፋብሪካና በአዳማ የሚገኙት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ይወገዳሉ።

በኢትዮጵያ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ 460 መጋዘኖች ከ1 ሺህ 400 ሜትሪክ ቶን በላይ ዲዲቲ ኬሚካል እንደሚገኝ ኢዜአ ዘግቧል።