ኮርፖሬሽኑ የባቡር ማሰልጠኛ አካዳሚ ሊገነባ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥር 5 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የባቡር ማሰልጠኛ አካዳሚ ግንባታ ሊጀምር ነው።

ኮርፖሬሽኑ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ግንባታው ከቻይና መንግስት በተገኘ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ እርዳታ የሚገነባ መሆኑን አስታውቋል። 

የኮርፖሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ደረጀ ተፈራ፥ አካዳሚው ስልጠና ሲጀምር ሙሉ በሙሉ በኮርፖሬሽኑ አቅምና ባለሙያዎች እንደሚያሰለጥን ተናግረዋል።
በ2011 መስከረም ወር ላይ በቢሾፍቱ ከተማ በ157 ነጥብ 7 ሄክታር መሬት ላይ የሚጀመረው የአካዳሚው ግንባታ በ2 አመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሏል።
የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው ሲጠናቀቅ እስከ 1 ሺህ የሚደርሱ ሰልጣኞችን በቴክኒከ እና ሙያ በሰባት ልዩ ልዩ የስልጠና መስኮች ያሰለጥናል።
ሙሉ በሙሉ ግንባታው ሲጠናቀቅም 3 ሺህ ተማሪዎችን ከሃገር ውስጥና ከውጪ ሃገራት ተቀብሎ ያሰለጥናል ነው የተባለው።
አካዳሚው የንድፈ ሃሳብ እና የተግባር ልምምድ የሚሰጥበት እስከ 800 ሜትር ርዝመት ያለው የባቡር መስመር የሚዘረጋለት ሲሆን፥ ግንባታው በቻይና ተቋራጭ ይከናወናል።
የስርዓተ ትምህርቱ ዝግጅት ቀደም ሲል በውጭ ሀገራት ሰልጥነው በተመለሱ የሀገር ውስጥ ባለሙያዎች እንደሚሰራም ተገልጿል።


በኤርሚያስ ፍቅሬ