ሩሲያ በክሬሚያ ከምድር ወደ አየር ተወንጫፊ ፀረ ሚሳኤል መሳሪያ ተከለች

አዲስ አበባ ፣ ጥር 5 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ በክሬሚያ ከምድር ወደ አየር ተወንጫፊ ፀረ ሚሳኤል መሳሪያ መትከሏ ተሰማ።

የሃገሪቱ ሚዲያዎች እንደዘገቡት ሞስኮ ኤስ 400 የተሰኙና ከምድር ወደ አየር የሚወነጨፉ ፀረ ሚሳኤል መሪያዎችን በዛሬው እለት ተክላለች።

የአሁኑ ፀረ ሚሳኤል መሳሪያ ተከላ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑንም መረጃዎች ያመላክታሉ።

በተጠናቀቀው 2017 የፀደይ ወቅት የመጀመሪያውን ኤስ 400 ሚሳኤል በወደቧ ፌዶሲያ ከተማ መትከሏ ይታወሳል።

መሳሪያዎቹ በአነስተኛዋ የሴቫስቶፖል ከተማ የተተከሉ ሲሆን፥ ሞስኮ ከዩክሬን የሚያዋስናትን የአየር ክልል ለመቆጣጠር ይውላሉ ነው የተባለው።

የሩሲያን የአየር ሃይል አዛዥ የጠቀሰው የኢንተርፋክስ ዘገባ ደግሞ ሚሳኤሎች አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ጊዜ በ5 ደቂቃዎች ውስጥ ከመከላከል ወደ ማጥቃት መሸጋገር እንደሚችሉ ገልጿል።

በ400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለን የአየር ላይ ኢላማን እንዲሁም በ60 ኪሎ ሜትር ውስጥ የሚገኝን ባለስቲክ ሚሳኤል ማውደም የሚችሉ ናቸው።

 

የቀድሞዋ ዩክሬን ግዛት ክሬሚያ ከፈረንጆቹ 2014 ጀምሮ በሩሲያ ቁጥጥር ስር ትገኛለች።

ከዚያን ጊዜ ወዲህም ሞስኮ ሊቃጣ ይችላል ያለችውን ጥቃት ለመመከት በሚል በስፍራው ወታደሯን ስታደራጅ ቆይታለች።

የአውሮፓ ህብረትና አሜሪካ ደግሞ ይህን የሞስኮን ድርጊት ህገ ውጥ በማለት ይኮንኑታል፤ በሃገሪቱ ላይም ተደጋጋሚ ማዕቀቦችን ጥለዋል።

 

 


ምንጭ፦ ሬውተርስ