በኦሮሚያ ክልል በ9 ሆስፒታሎችና 61 ጤና ጣቢያዎች የማስፋፊያ ግንባታ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥር 4 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የጤና አገልግሎትን ጥራት እና ደረጃ ለማሳደግ በዘጠኝ ሆስፒታሎች እና 61 ጤና ጣቢያዎች የማስፋፊያ ግንባታ ሊካሄድ ነው።

በክልሉ ያለውን የጤና አገልግሎት ጥራትና ደረጃ ለማሳደግ የክልሉ ጤና ቢሮ እና የፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በነባር ሆስፒታሎች የማስፋፊያ ስራ እያከናወኑ ይገኛል።

የሆስፒታሎቹ ማስፋፊያ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ባለባቸውና ቅሬታ በሚሰማባቸው ቦታዎች ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተገነባ ሲሆን፥ በተያዘው በጀት ዓመት የዲዛይንና ሌሎች ተያያዥ ስራዎችን በመጨረስ ወደ ስራ ለማስገባት እቅድ ተይዞላቸዋል።

የማስፋፊያ ግንባታው በጭሮ፣ ጌዶ እና ደምቢዶሎ ጠቅላላ ሆስፒታሎች እና በቢሾፍቱ፣ አዶላ ዋዩ፣ ነገሌ እና ሞያሌ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ተናግረዋል፡፡

ሆስፒታሎቹ የጽኑ ህሙማን ማቆያ፣ የቀዶ ህክምና አገልግሎት እና በአዲስ መልኩ መስጠት የሚጀምረው የስነ አእምሮ ህክምናን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችም የሚያካትቱ ይሆናል፡፡

ለዘጠኙ ሆስፒታሎች 500 ሚሊየን ብር በጀት የተያዘ ሲሆን በፌደራል እና በክልሉ መንግስት የሚሸፈን ነው፡፡

ማስፋፊያ የሚደረግላቸው ሆስፒታሎች በተያዘላቸው ጊዜ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩም የቅድመ ዝግጅት ስራ በጥንቃቄ መከናውኑንም ዶክተር ደረጄ ይናገራሉ።

ከሆስፒታሎች በተጨማሪም የ61 ጤና ጣቢያዎች የማስፋፊያ ስራም ይካሄዳል፤ ማስፋፊያው ከፍተኛ የአገልግሎት መጨናነቅ በሚታይባቸው የአርብቶ አደር አካባቢዎች የሚካሄድ ነው ተብሏል።

150 ሚሊየን ብር ለሚጠይቀው የማስፋፊያ ስራም አሁን ላይ ማስፋፊያ የሚደረግባቸው ጤና ጣቢያዎች ልየታ ስራ እየተከናወነ ነው።

በክልሉ ባለፈው ዓመት በ400 ሚሊየን ብር ወጪ የማስፋፊያ ግንባታ የተጀመረባቸው 11 ሆስፒታሎችም በዚህ አመት ይጠናቀቃሉ ተብሏል፡፡

በተጨማሪም በ252 ጤና ጣቢያዎች ላይም የማስፋፊያ ስራ እየተካሄደ መሆኑንም ሃላፊው ገልጸዋል።

የእነዚህ ማስፋፊያ ስራዎች አብዛኛዎቹ ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ ሲሆን፥ በሚቀጥለው አመት በሙሉ አቅም አገልግሎት መሰጠት ይጀምራሉ ነው የተባለው፡፡

በክልሉ ተጨማሪ ሆስፒታሎችን ከመገንባት ባሻገር ያሉትን በህክምና መሳሪያዎችም ሆነ በሰው ሀይል የማሟላት ስራም ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑንም ነው ሃላፊው የገለጹት።

 

በሰርካለም ጌታቸው