የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በመዲናዋ ከ16 ሺህ በላይ ቤቶች እንደሚገነባ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ከ16 ሺህ በላይ ቤቶችን ሊገነባ መሆኑን አስታወቀ።

ኮርፖሬሽኑ ለቤቶቹ የግንባታ ስራ የዲዛይን ክለሳ፣ የአዳዲስ ዲዛይኖችና የአፈር ምርመራ ስራዎችን ለማከናወን ከተመረጡ ድርጅቶች ጋር ዛሬ ተፈራርሟል።

ኮርፖሬሽኑ ስምምነቱን የተፈራረመው ኖሚ ኢንጂነሪንግ ኃላፊነቱ የወሰነ የግል ማህበር እና ጂ አይ አማካሪ ድርጅት ጋር ነው።

ድርጅቶቹ ለግንባታው የሚረዳ የዲዛይንና የአፈር ምርመራ ስራዎችን በተመረጡ ተቋማት ይዞታ ስር ባሉና ከከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ አዳዲስ ቦታዎች ያከናውናሉ።

ቤቶቹ ከ35 ሜትር በላይ ከፍታና ባለ 9 ወለል ሲሆኑ፥ ከ1 እስከ 4 መኝታ ክፍሎች ይኖራቸዋል።

በኮርፖሬሽኑ የቤቶች ልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ግሩም ብርሃኑ እንደገለጹት የዲዛይንና የአፈር ምርምር ስራው በሁሉት ወራት ውስጥ ተጠናቆ በተያዘው ዓመት መጨረሻ የቤቶቹ ግንባታ ይጀመራል።


በሀብታሙ ተክለስላሴ