ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የእንግሊዝ ጉብኝታቸውን ሰረዙ

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእንግሊዝ ሊያደርጉት የነበረውን ጉብኝት መሰረዛቸው አስታውቀዋል።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የፊታችን የካቲት ለመማድረግ በነበረው ጉብኝት በለንደን ከተማ በ1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የተገነባውን አዲሱን የአሜሪካ ኤምባሲ መርቀው እንደሚከፍቱ ይጠበቅ ነበር።

ፕሬዚዳንቱ በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍም፥ “ከለንደን ሜይፌይር ወደ ደቡብ ለንደን የተቀየረውን አዲሱን ኤምባሲ ብዙም አልወደድኩትም” ብለዋል።

“የቀድሞ ኤምባሲ በቀድሞ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ለማይረባ ነገር ተሸጧል” ሲሉም ፕሬዚዳንቱ በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።

ፕሬዚዳንቱ የፊታችን የካቲት ወር በለንደን ሊያካሂዱት አስበው የነበረው ጉብኝት በእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ የቀረበ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እንዳልነበረም ተነግሯል።

የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጉብኝትን መሰረዝ ላይ የእንግሊዝ መንግስት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።

ፕሬዚዳንቱ ለመቅረታቸው ኤምባሲውን መክፈት ስለማይፈልጉ መሆኑን ቢጠቅሱም፤ በለንደን አውራ ጎዳናዎች ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ሊደርስባቸው ይችላል በሚል ስጋት ጉብኝቱ ሳይሰረዝ እንዳልቀረ ነው እየተነገረ ያለው።

የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የየካቲት ወር ጉብኝት መርሃ ግብር ውስጥ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ ጋር መወያየት እና ከእንግሊዟ ንግስት ጋር ምሳ መብላት ተካቶበት እንደበረም ተነግሯል።

ዶናልድ ትራምፕ ኤምባሲውን ለመመረቅ ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ተከትሎም የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን የኤምባሲውን ሪባን ቆርጠው ሊመርቁ ይችላሉ ተብሏል።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባሳለፍነው ዓመት ከእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ ጋር ተገናኝተው በተወያዩበት ወቅት ነበር ከእንግሊዟ ንግስት የቀረበላቸውን ግብዣ የተቀበሉት።

ይህንን ተከትሎም 1 ነጥብ 8 ሚሊየን እንግሊዛውያን ፕሬዚዳንቱ እንግሊዝን መጎብኘት የለባቸውም የሚለው የፊርማ ማሰባሰብ ላይ ፈርመው የነበረ ሲሆን፥ ጉዳዩም ለሀገሩቱ ፓርላማ ቀርቦ ክርክር ተካሂዶበት እንደነበረ ይታወሳል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ