በአዲስ አበባ ከ16 በላይ አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሊጀመር ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከ16 በላይ አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሊጀመር ነው።

ለመንገዶቹ ግንባታ ከ4 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ በጀት መመደቡን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን አስታውቋል።

በዚህ አመት ግንባታቸው ከሚጀመሩት ፕሮጀክቶች ውስጥ የ8 መንገዶች ግንባታ ስምምነትም መፈረሙን የባለስልጣኑ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጥኡማይ ወልደገብርኤል ተናግረዋል።።

እነዚህ ስምምነታቸው የተፈረሙት መንገዶች ከ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የሚጠይቁ ሲሆን ከ 24 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው ናቸው።

ስምምነት ከተፈረመባቸው መንገዶች ውስጥ ከሀይሌ ጋርመንት እስከ ጀሞ አደባባይ፣ ቄራ ከብት በረት እስከ ጎፋ መብራት ሀይል፣ ቦሌ አያት ሳይት 4 ኮንዶሚኒየም ይገኙበታል።

በጨረታ ሂደት ላይ ከሚገኙት መንገዶች ውስጥ ደግሞ ከቦሌ መድሀኒያለም 22 ማዞሪያ እንግሊዝ ኤምባሲ፣ ከአየር ጤና ወለቴ፣ ከራስ ደስታ ሆስፒታል እስከ ቀጨኔ መድሀኒያለም ኮተቤ ኪዳነምህረት ኮተቤ ደህንነት መንገዶች ይገኙበታል።

እነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች እንደ ርዝመታቸው ከ1 እስከ 2 ዓመት ተኩል የግንባታ ጊዜ ተቀምጦላቸዋል።

 

በዙፋን ካሳሁን