የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ የ17 አመራሮች ሽግሽግ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2010(ኤፍ.ቢ.ሲ) ክልሉን የሚመራው የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ(ሐብሊ) የሕብረተሰቡን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣሉ ያላቸውን የ17 አመራሮች ሽግሽግ አደረገ፡፡

የሊጉ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ያሲን ሁሴን እንደገለጹት፥ የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ሕብረተሰቡን በየደረጃው ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤቶችን አስመዝግቧል።

በህዝብ ተሳትፎ በየፈርጁ የተመዘገበው ውጤት አበረታች ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የድርጅቱን ስኬት ወደ ኋላ ሊቀለብሱ የሚችሉ የኪራይ ሰብሳቢነት እና የመልካም አስተዳደር ችግር የወለዳቸው እንቅፋቶች መስተዋል ጀምረዋል።

ድርጅቱ ይህን በሚገባ በመረዳት ጥንካሬዎቹን ለማስቀጠል እና ደካማ ጎኖችን ለማረም እንዲሁም ከልማቱ ጋር እያደገ የመጣውን የሕብረተሰቡን ጥያቄ ለማስተናገድ የሚያስችለውን ግምገማ ለበርካታ ቀናት አካሂዷል።

በጥልቅ ተሃድሶ ግምገማም በየደረጃው ከፍተኛ ትግልን የሚሹ የመልካም አስተዳደር እና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች ከነመፍትሄዎቻቸው ተለይተው የእርምት እርምጃ መወሰዱን ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ያሲን ገልጸዋል።

በእዚህም በተለያዩ የስልጣን እርከን ላይ የሚገኙ አመራሮችን ብቃት እና ጥንካሬን በመለየት በተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት የአመራር ሽግሽግ መደረጉን ጠቁመዋል።

አመራሮቹ በተመደቡበት የሥራ መደብና ተቋም ህዝብ የጣለባቸውን አደራ በብቃት መወጣት እንደሚችሉ ድርጅቱ እምነት የጣለባቸው መሆኑን አቶ ያሲን ጠቁመው፥ በቀጣይ ቀናትም ተመሳሳይ የሆነ የአመራር ሽግሽግ በወረዳዎች እንደሚካሄድ አክለው ገልጸዋል።

በከተማው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት፥ ድርጅቱ ያደረገው የጥልቅ ተሀድሶ ግምገማ መልካም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠልና በገጽታ ግንባታ ሥራዎች ላይ ተሿሚዎቹ በትኩረት መስራት እንዳለባቸውም አመልክቷል።

በተደረገው የአመራር ሽግሽግም:-
1. አቶ ፈቲ ረመዳን የክልሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ

2. አቶ ኦርዲን በድሪ የክልሉ የባህል ቅርስና ቱሪዝም ኃላፊ

3. አቶ መሀመድ ኑረዲን የከተማው የመዘጋጃ ቤት ሹም

4. አቶ መሀመድ ዘከርያ የፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ

5. ወይዘሮ ሽኩርያ አህመድ የፕሬዚዳንቱ ልዩ አማካሪ

6. አቶ አብዱላዚዝ አደም የክልሉ የልህቀት ማዕከል ኃላፊ

7. አቶ ካሊድ አልዋን የክልሉ ብዙሀን መገናኛ ኤጀንሲ ኃላፊ

8. አቶ ፈቲህ መሃዲ የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ምክትል ኃላፊ

9. አቶ ተወለደ አብዶሽ የክልሉ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ኃላፊ

10. አቶ ኢሊ አብዱልረሂም የቤቶች ልማትና የመንግስት ኮንስትራክሽን ኃላፊ

11. አቶ መሀመድ አብደላ የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ኃላፊ

12. አቶ አብዱልሃኪም አብዲ የፕሬዚዳንቱ የማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ

13. አቶ አሪፍ መሀመድ የፕሬዚዳንቱ የግብርና ዘርፍ አማካሪ

14. አቶ አብዱልአዚዝ መሀመድ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ

15. አቶ አብደላ አህመድ የደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ኃላፊ

16. አቶ ያሲን ዮኒስ የጁገል ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ

17. አቶ ሁሄዲን አህመድ የፕሬዚዳንቱ የህዝብ ግንኙነት አማካሪ ሆነው ተመድበዋል።

 

 

ምንጭ፦ ኢዜአ