በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ የጥርስ ህክምና ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ እጥረት ችግር እንደፈጠረባቸው ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በተለያዩ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች እየተማሩ የሚገኙ የጥርሰ ህክምና ተማሪዎች ትምህርታቸውን በተገቢው ደረጃ እየተማሩ እንዳልሆነ ተናገሩ።

የጥርሰ ህክምና ትምህርት በአዲስ አበባ፣ መቐለ እና ጅማ ዩኒቨርሲቲዎች ይሰጣል።

በእነዚህ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ እየሰለጠኑ ያሉት ተማሪዎች የመማር ማስተማር ሂደቱ ችግሮች የበዙበት እንደሆነ ይናገራሉ።

ቅሬታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያቀረቡት ተማሪዎች በሰው ሀይልም ሆነ በቁሳቁሰ እጥረት ሳቢያ የሚያገኙት በተግባር ያልተደገፈ ስልጠና በነገው ማንነታቸው ላይ ስጋት እንደፈጠረ ነው የሚናገሩት።

በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የ5ኛ ዓመት ተማሪዎች ፕሮስቶ ዶንቲክስ ወይም የአርቲፊሻል ጥርስን የመስራት እና የመትከል የትምህርት ክፍል ተማሪዎች ትምህርቱን ከቀለም ውጭ በተግባር አናውቀውም ይላሉ።

በጉዳዩ ዙሪያ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ እና መቐለ ዩኒቨርሲቲ የስራ ሀላፊዎች በሰጡት ምላሽ ችግሩ ሀገር አቀፍ ነው ብለዋል፡፡

በተለይ የቁሳቁስ እና የሰው ሀይል እጥረቱ ለትምህርት ዘርፍ እድገቱ ማነቆ እንደሆነም አስረድተዋል።

ችግሩ አለ የሚሉት በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የጥርስ ህክምና ትምህርት ክፍል ሀላፊ ዶክተር መለሰ ታቦር፥ ችግሩ ገበያ ላይ የቁሳቁስ እጥረት በመኖሩ እንደተፈጠረ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥርስ ህክምና ማዕከል ሀላፊ እና መምህር ዶክተር ወንድወሰን ፋንታዬ በበኩላቸው፥ የቁሳቁስ እጥረቱን የምንቀርፈው በውጭ ሀገር ድጎማዎች ነው ብለዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ የሰው ሀይል ችግሩን ለማቃለል በዩኒቨርሲቲዎቹ በኩል ከውጭ መምህራንን መቅጠር እንደመፍትሄ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።

ለዘለቄታው ግን በሀገር ውስጥ የድህረ ምረቃ ትምህርት እንዲሰጥ ማድረግና የባለሙያውን አቅም ማሳደግ ላይ ትኩረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የጥርስ ህክምና ባለሙያዎች ማህበርም፥ የቁሳቁስ ችግሩን ለመቀነስ እና የአቅራቢዎችን ቁጥር ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራሁ ነው ብሏል።

ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከተቋማቱ ጋር በቅርበት ለመስራት እና ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ ከግብዓት ጋር በተያያዘ ከዩኒቨርሲቲዎቹ አቅም በላይ የሆነ ችግር ካለ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ችግሩ መፍትሄ እንዲያገኙ ይሰራል ነው ያለው።

 

በቤተልሄም ጥጋቡ