በጉራ ፈርዳ ወረዳ የሚኖሩ የሌላ ክልል ተወላጆችን በመግደልና መሬታቸውን በመቀማት የተከሰሰው ግለሰብ በእስራት ተቀጣ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 2 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤንች ማጂ ዞን የጉራ ፈርዳ ወረዳ ከግብረ አበሮቹ ጋር በመደራጀት በአካባቢው የሚኖሩ 38 የሌላ ክልል ተወላጆችን በመግደልና መሬታቸውን በመቀማት የተከሰሰው ግለሰብ በ15 አመት ፅኑ እስራት ተቀጣ።

ተከሳሽ ጋቡስ ፋጢ በዞኑ ጉራ ፈርዳ ነዋሪ ሲሆን፥ ወንጀሉን 17 ከሚደርሱ የስራ ሃላፊዎችና ግለሰቦች ጋር በመሆን መፈጸሙን የአቃቢ ህግ ክስ ያመላክታል።

ተከሳሹ ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን በወረዳው በሚገኙ ቀበሌዎች ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመምጣት የሰፈሩ ግለሰቦችን መሬታችንን ለቀው ይውጡ በማለት በመደራጀትና የጦር መሳሪያ በመታጠቅ ጫካ መግባቱም በክሱ ተጠቅሷል።

በእነዚህ ጊዜያትም ከሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎች በመምጣት በሰፈሩ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም ግድያና የአካል ጉዳት አድርሷል ነው የተባለው።

ከመስከረም 25 ቀን እስከ ጥቅምት መጨረሻ 2007 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥም የተፈጠረውን ግጭት ለማረጋጋት በተንቀሳቀሱ 12 የፌደራል ፖሊስ አባላት ላይ ግድያ መፈጸሙም ነው በክሱ የተጠቀሰው።

ከ12 የፌደራል ፖሊሶች በተጨማሪም 38 በአካባቢው የሚኖሩ የተለያዩ ብሄረሰብ አባላት ላይ የግድያ ወንጀል በመፈጸም 4 ግለሰቦችን ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን ማቁሰሉንም አቃቢ ህግ በክሱ አስረድቷል።

ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆንም ከ16 ሺህ በላይ የቤት እንስሳትና ከ12 ሺህ በላይ ቤቶችን በማውደም፥ ሌሎች ጉዳቶች እንዲደርሱ ማድረጉንም አቃቢ ህግ በክሱ አመላክቷል።።

ተከሳሹ ጋቡስ ፋጢ አቃቢ ህግ ያቀረበበትን የሰነድና የሰው ምስክር ማስተባበል ባለመቻሉም፥ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ የወንጀል ችሎት ጥፋተኛ ብሎታል።

በዛሬው እለትም በ15 አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ አስተላልፏል።

 


በታሪክ አዱኛ