የትግራይ ክልል የስነ ምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን በክልሉ ያለአግባብ የተወሰዱ መሬትና ንብረትን በመንግስት እንዲወረስ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የትግራይ ክልል የስነ ምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን በክልሉ ያለአግባብ የተወሰዱ መሬትና ንብረትን በመንግስት እንዲወረስ ማድረጉን አስታወቀ።

መዚህም መሰረት 7 ሚሊየን 95 ሺህ በላይ ብር በመንግስት እንዲወረስ መደረጉ ተገልጿል።

የክልሉ የስነ ምግባርና ጸረሙስና ኮሚሽን ለፋና ብሮድካስቲግ ኮርፖሬት እንደገለፀው፥ በተያዘው በጀት ዓመት በስድስት ወራት በፍርድ ቤት በተሰጠ ውሳኔ መሰረት ነው ገንዘቡ እንዲወረስ የተደረገው።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ወልደገብርኤል ወለድማርያም፥ በፍርድ ቤት በተሰጠ የፍትሃ ብሄር ውሳኔ መሰረት ከተወረሱት መካከል በኮረም ከተማ 175 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ያለአግባብ የተያዘ ህንጻና በተመሳሳይ በአደዋ ከተማ ያለአግባብ የተወሰደ 637 ካሬ ሜትር ይዞታ ይገኙበታል።

ከፍትሃ ብሄር በተጨማሪ ኮሚሽኑ በተለያዩ ወንጀሎች ክስ በመሰረተባቸው 78 ተከሳሾች ላይ ከ1 ዓመት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ማስቀጣቱን አስታውቋል።

በወንጀል ብቻ 411 ሺህ ብር በላይ ከተከሳሾች በቅጣት የተሰበሰበ ብር መኖሩንም ኮሚሽኑ ገልጿል።


በታሪክ አዱኛ