ኢትዮጵያና ኩባ ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለፁ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2010(ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ እና ኩባ ግንኙነታቸን የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ።

በኩባ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ከኩባው ፕሬዚዳንት ራውል ካስትሮ ጋር በትናንትናው እለት ተገናኝተው ተወያይተዋል።

ውይይቱን ተከትሎ የኩባ መንግስት ባወጣው መግለጫም፥ በሁለቱ ፕሬዚዳንቶች መካከል የተደረገውን ስብሰባ የወንድማማቾች ውይይት ብሎታል።

ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች በቆይታቸው፥ በሁለትዮሽ፣ በፖለቲካ እና በተለያዩ ሊተባበሩባቸው በሚችሉባቸው ዘርፎች ላይ መወያየታቸውም በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

በውይይታቸውም በሀገራቱ መካከል የነበረውን ግንኙነት በአዲስ መልክ የበለጠ ለማሳደግ ፍላጎት ማሳየታቸው እና መስማማተቸው ተገልጿል።

ፕሬዚዳንት ሙላቱ እና ካስትሮ በሌሎች ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ መወያየታቸውን የኩባ መንግስት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ባሳለፍነው ማክሰኞ የኩባ ጉብኝታቸውን የጀመሩት ፕሬዚዳንት ሙላቱ በኮሎን ናርኮፖሊስ የሚገኘው የሀገሪቱ ባለስልጣናት፣ ባለውለታዎች እና የጦር ጀግኖች የመቃብር ስፍራ ተገኝተው የአበባ ጉንጉን አኑረዋል።

cuba1.jpg

በዚሁ ጊዜም ለኢትዮጵያ ነጻነት ህይወታቸውን የሰው የኩባ ወታደሮችን አስታውሰዋል።

የኩባ የቀድሞ አብዮት መሪ እና የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት ፊደል ካስትሮ፥ ሁሌም ለነፃነት የሚታገሉ መሪ ነበሩ ሲሉም ገልፀዋል።

እስከ ፊታችን አርብ ጥር 4 በኩባ ጉብኝት የሚያደርጉት ፕሬዚዳንቱ፥ በኢትዮጵያ እና በኩባ መካከል ያለው የቆየ ግንኙነት በኢንቨስትመንት እና በሌሎች የትብብር መስኮች ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በሁለቱ ሀገራት ከዚህ ቀደም በጤና እና በግብርና ዘርፎች በጋራ ሲሰሩ የነበረ ሲሆን፥ በቀጣይም በትምህርት እና በባዮ ቴክኖሎጂ ዘርፎች በጋራ እንደሚሰሩ ተገልጿል።
ኢትዮጵያና ኩባ ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዳላቸው ይነገራል።

ኩባውያንም ኢትዮጵያውያን ለነጻነት ባደረጉት ተጋድሎ አጋርነታቸውን አሳይተዋል።

በተለይም የዚያድባሬዋ ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት የሃገሪቱ መሪ ፊደል ካስትሮ አጋርነታቸውን በማሳየት ኢትዮጵያን በጦርነቱ አግዘዋል።

በወቅቱ በሺህ የሚቆጠር ሰራዊት በመላክና የተለያዩ ወታደራዊ ድጋፎችን በማድረግ ኢትዮጵያውያን ድሉን እንዲቀዳጁ ማገዛቸውም የሚታወስ ነው።