የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን አይ ኪ ያ በተሰኘ ኩባንያ ላይ ከግብር ጋር በተያያዘ ማጣራት ሊያደርግ ነው

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 9 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን አይ ኪ ያ በተሰኘ የቤትና የቢሮ እቃዎች አምራች ኩባንያ ላይ ከግብር ጋር በተያያዘ ማጣራት ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ መሰረቱን ኔዘርላንድስ ያደረገው የስዊድን ኩባንያ በኔዘርላንድ መንግስት ያልተገባ የግብር ማበረታቻ አግኝቷል የሚል እምነት እንዳለው ገልጿል።

ይህን ተከትሎም ኩባንያው በተባለው መልኩ ያልተገባ የግብር ማበረታቻ ስለማግኘት አለማግኘቱ ማጣራት አደርጋለሁ ብሏል።

ከዚህ ባለፈም ኩባንያው የህብረቱን የንግድ ህጎች መጣስ አለመጣሱን አልያም የኔዘርላንድ መንግስት ድጋፍ እንደተደረገለት እንደሚያጣራም ነው የገለጸው።

በህብረቱ የንግድ ውድድር ኮሚሽነር ማርጋሬት ቬስታገር ማንኛውም ኩባንያ የሚጠበቅበትን ግብር መክፈል እንዳለበት ተናግረዋል።

በአውሮፓ ህብረት ህግ መሰረት ሃገራት ለተወሰኑ ኩባንያዎች ብቻ ለይተው የግብር ማበረታቻ ማድረግ አይችሉም።


ምንጭ፦ ቢቢሲ