ራማፎሳ የደቡብ አፍሪካው ገዥ ፓርቲ ሊቀ መንበር ሆነው ተመረጡ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 9 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ሲሪል ራማፎሳ የደቡብ አፍሪካው ገዥ ፓርቲ አፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ (ኤ ኤን ሲ) ፓርቲ ሊቀ መንበር ሆነው ተመረጡ።

ፓርቲው ያካሄደው የሃገሪቱን ፕሬዚዳንትና የፓርቲውን ሊቀ መንበር ጃኮብ ዙማን የሚተካ አዲስ ሊቀ መንበር ምርጫ ውጤትን ምሽቱን ይፋ አድርጓል።

በዚህም ከበርቴው ራማፎሳ አዲሱ የኤ ኤን ሲ ፓርቲ ሊቀ መንበር ሆነው ተመርጠዋል።

ራማፎሳ ተፎካካሪያቸው ሆነው የቀረቡትንና የፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማን የቀድሞ ባለቤት ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማን አሸንፈዋል።

አዲሱን ሊቀ መንበር ለመምረጥ በተሰጠ ድምጽ ራማፎሳ 2 ሺህ 440 ድምጽ ሲያገኙ፥ ድላሚኒ ዙማ ደግሞ 2 ሺህ 261 ድምጽ በማግኘት ተሸናፊ ሆነዋል።

የምርጫ ውጤቱን ተከትሎም ከበርቴው ፖለቲከኛ በፈረንጆቹ 2019 ተቀማጩን ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማን የመተካት ሰፊ እድል አላቸው ተብሏል።

አሁን ላይ የሃገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን እያገለገሉ ያሉት ራማፎሳ የአፓርታይድን አገዛዝ ለመጣል በተደረገው ሂደት ጠንካራ ተሳትፎ እንደነበራቸው ይነገራል።

በወቅቱም የነጮችን የበላይነት ለመጣል በተደረገው ትግል ተሳትፎ በማድረግ ለእስር ተዳርገው ቆይተዋል።

ከአፓርታይድ አገዛዝ መወገድ በኋላ የወጣውን የደቡብ አፍሪካ ህገ መንግስት በማርቀቅና የህገ መንግስት አውጭውን ምክር ቤት በመምራት ግንባር ቀደም ሚና መጫወታቸውም ነው የሚነገረው።

በተለያዩ የህግ ሙያዎች እንዲሁም ዘግየት ብለውም የሃገሪቱ ፓርላማ አባል በመሆን አሁን ላይ ደግሞ የሃገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።

የዛሬውን የሊቀ መንበርነት ምርጫ ማሸነፋቸውን ተከትሎም ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማን ተክተው የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት የመሆን እድላቸው ሰፊ ነው ተብሏል።

ጃኮብ ዙማ የፕሬዚዳንትነት የስልጣን ጊዜያቸው በፈረንጆቹ 2019 የሚያበቃ ሲሆን፥ አዲሱን የሃገሪቱን መሪ ለመሰየምም ሃገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዋን በዚያው ወቅት ታካሂዳለች።

በርካቶችም ከበርቴው ፖለቲከኛ ሃገራቸውን ከጃኮብ ዙማ በኋላ መምራት የሚችሉበት እድል ሰፊ መሆኑን እየተናገሩ ነው።

ኤ ኤን ሲ ደቡብ አፍሪካን ከነጻነት ማግስት ላለፉት 23 አመታት እየመራት ይገኛል።

 

 


ምንጭ፦ ቢቢሲ