የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አዳዲስ ሹመቶችን አፀደቀ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 9 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አዲስ የቀረቡ የክልሉን ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የክልሉን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሹመት መርምሮ አጸደቀ።

ምክር ቤቱ በዛሬው አስቸኳይ ጉባኤው የከማሼ ዞን ዋና አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ አበራ ባየታን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደድርነት ሹመት አጽፅድቋል።

ከዚህ ባለፈም የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ሙለታ ወንበር የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እንዲሆኑ የቀረበውን ሹመትም አጽድቆታል።

የቀድሞው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አምባሳደር ምስጋና አድማሱ እና የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ፈቃዱ ታደሰ በክልሉ የተሃድሶ ግምገማና በራሳቸው ጥያቄ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን አስታውቀዋል።

አዳዳሶቹ አመራሮች በነበራቸው የአመራር ብቃት እና ባበረከቱት አስተዋጽኦ ምክንያት መመረጣቸውንም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ ከዚህ በተጨማሪ ስምንት የካቢኔ አባላትን፣ የከማሼ ዞን ዋና አስተዳዳሪንና የምክር ቤቱ የአቅም ግንባታና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሹመቶች ማጽደቁን ኢዜአ ዘግቧል።