በወልዲያና ጂማ ዩኒቨርሲቲዎች ተቋርጦ የነበረው የመማር ማስተማር ሂደት ተጀምሯል

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 9 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በወልዲያና ጅማ ዩኒቨርሲቲዎች ለጥቂት ቀናት ተቋርጦ የነበረው የመማር ማስተማር ሂደት ተጀምሯል።

በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ባለፈው ሳምንት ተፈጥሮ በነበረ ሁከት ሳቢያ የመማር ማስተማሩ ሂደቱ ተቋርጦ መቆየቱን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ያለው እንዳወቅ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው ሲማሩ ከነበሩ ተማሪዎች መካከልም ከ1 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑት ወደ ቤተሰቦቻቸው ተመልሰው ነበር።

ከዚህ ባለፈም በግቢው ውስጥ የነበሩ ተማሪዎች በከፍተኛ ስጋት ውስጥ በመሆናቸው የመማር ማስተማር ሂደቱ ተቋርጦ ቆይቷል ነው ያሉት።

ይሁን እንጅ ባለፉት አምስት ቀናት ችግሩን ለመለየትና የፀጥታ ሃይሉ በሰራው ሁኔታውን የማረጋጋት ስራ የመማር ማስተማር ሂደቱ መጀመሩን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

ባለፉት ቀናት የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና መምህራን ባደረጉት ተማሪዎችን የማወያየትና የማማከር ስራ የዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደት ወደነበረበት ሊመለስ መቻሉንም አስረድተዋል።

ማሪዎች ከስጋት ነጻ ይሆኑ ዘንድም መምህራን ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት ተማሪዎችን በስነ ልቦና በማነጽና አንድነትና ሰላምን እንዲያስተምሩ እንደሚደረግም አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲው ሰላምና መረጋጋቱ ወደነበረበት በመመለሱም ተማሪዎቹ ወደ መደበኛ ትምህርታቸው መመለሳቸውን በስፍራው ቅኝት እያደረገ ያለው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባልደረባ መታዘብ ችሏል።

በሁከቱ ከዩኒቨርሲቲው ወጥተው የነበሩ ተማሪዎችም እየተመለሱ መሆኑን ነው ባልደረባችን መታዘብ የቻለው።

ተማሪዎቹ በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተፈጥሮ የነበረውን ሁኔታ ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያዎች የተለቀቁት የጥላቻ መልዕክቶች ለግጭቱ መንስኤ እንደነበሩ ገልጸዋል።

በተፈጠረው ግጭት ሳቢያም በሰባት ተማሪዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት ሲደስርስ፥ አንድ የተማሪዎች የመማሪያ ህንጻም ጉዳት ደርሶበታል።

በተያያዘም በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተቋርጦ የነበረው የመማር ማስተማር ሂደት በሁሉም መስኮች ቀጥሎ እየተካሄደ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ለሜሳ ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቱ ከተማሪዎች ጋር በተደረገ ተከታታይ ውይይት እና ምክክር ለሁለት ሳምንታት ተቋርጦ የነበረው ትምህርት በመደበኛነት እየተካሄደ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በስጋት ወደ ቤተሰቦቻቸው የሄዱ ተማሪዎች ተመልሰው በትምህርት ገበታቸው ላይ እንደሚገኙ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፥ የማካካሻ ትምህርት እንዲያገኙ ለማድረግም በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲ የመውጫ ምዘና ፈተናና በሃገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ ከነበረው ግጭት ጋር በተያያዘ ጥያቄዎችን አንስተው የመማር ማስተማር ሂደቱ ተስተጓጉሎ ቆይቷል።

አሁን ላይ መደበኛው የመማር ማስተማር ሂደት ወደነበረበት የተመለሰ ሲሆን፥ ተማሪዎችም ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መልኩ በማቅረብ ሰላማዊ የትምህርት መርሀ ግብር እንዲቀጥል እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም መንግስት ፀጥታ የማስከበር ሃላፊነቱን እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

 

በሃይለኢየሱስ ስዩም እና በበላይ ተስፋዬ