በደቡብ ሱዳን ሰላም ላይ ትኩረት ያደረገ ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 9፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ትግበራ ከፍተኛ ባለድርሻ አካላት ጉባዔ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ባዘጋጀው ጉባዔ ላይም ሁሉም የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ተሳታፊ አካላት እና የሲቪክ ማህበራትን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የተለያዩ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃማትን፣ የኢጋድ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች በጉባዔው ላይ ተገኝተዋል።

በጉባዔው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፥ የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ሀይሎች ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው ለዜጎቻቸው ሰላም እና መረጋጋት መስራት አለባቸው ብለዋል።

ለደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ሀይሎች አሁን እየተደረገ ያለው የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት ጉባዔ የመጨረሻ አማራጭ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፥ ከዚህ በኋላ ወደ አስፈላጊው እርጃ ይገባልም ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃማት በበኩላቸው፥ የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ሀሎች የቀረበላቸውን የሰላም ስምምነት አማራጭ እንዲጠቀሙ ጠይቀዋል።

ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ከዚህ በኋላ በተፋላሚ ሀይላት መካከል የሚደረገው ሽምገላ ቆሞ ወደ ተግባር የሚገባበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ዛሬ የተጀመረው የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ትግበራ ከፍተኛ ባለድርሻ አካላት ጉባዔ ዛሬን ጨምሮ ለሚቀጥሉት አራት ቀናት ቀጥሎ ይካሄዳል።

ትኩረቱም የደቡብ ሱዳን የሰላም ሂደት ተግባራዊነት ላይ ያደረገው 59ኛየኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ በትናንትናው እለት መካሄዱ ይታወሳል።

የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ተግባራዊነትን የሚከታተለው አጣሪ እና መርማሪ ኮሚሽን ሊቀመንበር ፌስቱስ ሙጋዬ፥ በደቡብ ሱዳን ዙሪያ በዛሬው እለት የሚካሄደው ጉባዔ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ወሳኝ መሰረት ይሆናል ብለዋል።

አጣሪ እና መርማሪ ኮሚሽኑ በዛሬ ጉባዔ ላይ የትኩረት አቅጣጫ ሊሆኑ ይገባል ያላቸውን ሰባት ነጥቦችን የሚኒስትሮች ሰብሰባው ላይ አቅርቧል።

እነዚህም ግጭትና ጥላቻን በማስወገድ ተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ፣ ሁሉን አሳታፊ የፖለቲካ ውይይት ማካሄድ፣ የደህንነት አወቃቀሩን መፈተሽ፣ ግጭት ቀስቃሽ የሆኑትን አካላት ለህግ ማቅረብ ይገኙበታል።

እንዲሁም ሰብዓዊ እርዳታ በአግባቡ የሚደርስበትን ሁኔታ መፍጠር፣ የሽግግር መንግስቱ ማብቂያ ላይ ነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫ ማድረግ እና ለሰላም ስምምነቱ ተገዢ የማይሆኑ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ የሚሉት የትኩረት አቅጫ እንዲሁኑ ሊቀመንበሩ ፌስቱስ ሙጋዬ አቅርበዋል።

 

በስላባት ማናዬ