ቱርክ በምስራቅ እየሩሳሌም ኤምባሲ የመክፈት እቅድ አላት- ፕሬዚዳንት ኤርዶኻን

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ቱርክ በምስራቅ እየሩሳሌም ኤምባሲ የመክፈት እቅድ እንዳላት ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን አስታወቁ።

ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን እቅዳቸውን ይፋ ያደረጉት የሙስሊም ሀገራት መሪዎች ምስራቅ እየሩሳሌምን የፊሊስጤም ዋና ከተማ አድርጎ እውቅና እንዲሰጥ ጥሪ ካቀረቡ ከቀናት በኋላ ነው።

የሙስሊም ሀገራት ጉባዔም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማ በማድረግ እውቅና መስጠታቸውን ወድቅ ማድረጋቸው አይዘነጋም።

እስራኤም እየሩሳሌምን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሯ እና ከተማዋ ለሁለት የማትከፈል ነች ብላ ማሳወቋን ተከትሎም ፕሬዚዳንቱ የቱርክን ኤምባሲ በምን መልኩ ወደ ምስራቅ እየሩሳሌም ያዘዋውራሉ የሚለው ላይ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

የቱርኩ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን ለኤኬ ፓርቲ አባላት ባደረጉት ንግግር፥ በእየሩሳሌም የሚገኘው የቱርክ ቆንስላ ጀነራል ቀድሞውኑ በአምባሳደር የተወከለ ነው ብለዋል።

“እንደ ፈጣሪ ፈቃድ ኤምባሲያችንን በምስራቅ እየሩሳሌም የምንከፍትበት ቀን በጣም ቅርብ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማ በማድረግ እውቅና መስጠታቸውን ወድቅ ማድረግ በዋናነት እየተቃወሙ ካሉ መሪዎች ውስጥ የቱርኩ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን አንዱ ናቸው።

ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በሰጡት መግለጫም፥ አሜሪካ እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማናት በሚል የሰጠችው እውቅና የቀጠናውን ውጥረት ያባብብሰዋል ማለታቸው ይታወሳል።

የሙስሊም አለም ትብብር ድርጅት (ኦ አይ ሲ) አሜሪካ ለእየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማነት የሰጠችውን እውቅና እንደማይቀበል መግለፁም አይዘነጋም።

ምንጭ፦ www.reuters.com