ፕሬዚዳንት ፑቲን በመጪው ሳምንት በግብፅ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 28፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በመጪው ሳምንት በግብፅ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ክሬምሊን ገልጿል።

ፕሬዚዳንቱ በጉብኝታቸው ከግብፁ ፕሬዚዳን አብደል ፋታህ ኤል ሲሲ ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል።

ሁለቱ መሪዎች የሞስኮን እና የካይሮን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የሃይል አና የንግድ ግንኙነት በማጠናከር ዙሪያ እንደሚወያዩ ነው ክሬምሊን የጠቆመው።

ፑቲን ከመጪው ሰኞ ጀምሮ በሚያደርጉት ጉብኝት ከኤል ሲሲ ጋር በመካከለኛው ምስራቅ እና በሰሜን አፍሪካ የፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ።

ጉብኝቱ ሁለቱ ሀገራት ባሳለፍነው ሳምንት የሩሲያ የጦር አውሮፕላኖች የግብፅን ወታደራዊ ጣቢያ እንዲጠቀሙ ለመስማማታቸው ማቀዳቸውን ይፋ መሆኑን ተከትሎ የመጣ ነው።

ስምምነቱ ከሶሪያ ወታደራዊ ዘመቻዋ በኋላ ሩሲያ ወታደራዊ ሃይሏን በቀጠናው በስፋት ለማስገባት የምታደርገው ጥረት አንድ አካል ነው ተብሏል።

ግብፅ ፕሬዚዳንት ኤል ሲሲ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ከሩሲያ ጋር ያላትን ወታደራዊ ግንኙነት ያጠናከረች ሲሆን፥ የሩሲያ የጦር መሳሪያዎችን ለመግዛት መስማማቷ ይታወቃል ሲል አሶሺየትድ ፕሬስን ጠቅሶ ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል።