ህገ መንግስቱ ያስቀመጣቸውን ግዴታዎች አለመፈፀም የወቅቱ ስጋት ይሆን?

አዲስ አበባ፣ ህዳር 28፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) “ለበርካታ ጥያቄዎች ምላሽ ለሰጠው ህገ መንግስት ልዕልና በመቆም፥ ሀገሪቱ እያስመዘገበችው ያለው እድገት ማስቀጠል የሁሉም ሀላፊነት ነው” ይላሉ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው ምሁራን።

በአዲስ አበባ እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች መምህር የሆኑት እነዚህ ምሁራን፥ በአሁኑ ወቅት የሚስተዋሉ ችግሮች ህገ መንግስቱን ሙሉ በሙሉ ካለማክበር የመጡ መሆናቸውን ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ ያላት ህገ መንግስት እና የምትከተለው የፌደራሊዝም ስርዓት በርካቶች በአደባባይ እንደሚናገሩለት ባለፉት ዓመታት በርካታ ውጤቶችን አስመዝግቧል።

ይህ ህገ መንግስት በሀገሪቱ ከአሁን በፊት ይነሱ የነበሩ የማንነት ጥያቄዎች በህግ አግባብ እንዲፈቱ እና እውቅና እንዲያገኙ እያደረገ በመጓዝ ላይ መሆኑን ምሁራኑ ያነሳሉ።

ይህ አካሄድ ብሄር ብሄረሰቦች በራሳቸው ማንነት ተከብረው ለሀገር አንድነት የሚቆሙበት መድረክ የፈጠረ መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ እና አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር እና የአሜሪካው ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የጥናት ክፍል ባልደረባ አቶ አባይ ይመር ገልፀዋል።

በዚህም አሁን ላይ ያለው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ከአሁን በፊት የሀገሪቱ ዜጎች ለበርካታ ዘመናት ሲያነሷቸው ለነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠ መሆኑን ነው ያነሱት።

የአንድ ሀገር ህገ መንግስት ጥንካሬ የሚለካበት የራሱ የሆኑ መስፈርቶች አሉት፤ ከእነዚህ ወሳኝ መለኪያዎች መካከል ችግር ሲፈጠር እንዴት መፍታት እንደሚቻል የዛሬን እና የወደፊት ስጋቶችን በስፋት ተንትኖ ማስቀመጥ መቻሉ አንዱ ነው።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህገ መንግስት ጉዳዮች ረዳት ፕሮፈሰሩ ወንድወሰን ዋኬኔ፥ የኢፌዴሪ ህግ መንግስት ከበፊቶቹ በዓይነቱም በአላማውም ሁሉንም የሀገሪቱ ዜጎች አሳታፊ እና ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑን ይገልፃሉ።

ህገ መንግስት በአንዲት ሀገር ውስጥ ያሉ ዜጎችን አንድ የሚያደርግ እና ለአንድነታቸው መጠናከር ዋና ምስሶ ሆኖ የሚነሳ ቀዳሚ መሳሪያ ነው ይላሉ ረዳት ፕሮፌሰር ወንድወሰን።

አሁን ላይ በዚህ የኢትዮጵያ የፌደራሊዝም ስርዓት እና ህገ መንግስት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች እና የሚነሱ ጥያቄዎች ህግ መንግሰቱን ካለማክበር የሚፈጠሩ ችግሮች ናቸው ብለዋል።

እርሳቸው በዚህ የሀገሪቱ ጉዞ ውስጥ ትልቅ ውጤት የተመዘገበ ቢሆንም፥ አሁን ላይ እንደ ስጋት የሚታያቸው ለህገ መንግስቱ ልዕልና ሁሉም ባለድርሻ አካላት በሚፈለግባቸው ደረጃ ያለማክበር እና ያለመገንዘብ ጉዳይ ነው ሲሉም ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ምሁር አቶ አባይ፥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ጥያቄዎች መነሳት መጀመራቸው ህገ መንግስቱ ያመጣቸውን መብቶች እና ጥቅሞች አሟጦ የመጠቀም አዝማሚያ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

ከዚህ ባለፈም በየጊዜው እያደገ የመጣው የአዲሱ ትውልድ ወቅታዊ ፍላጎት ከግንዛቤ መግባት እንዳለበት በአንክሮ ተናግረዋል።

አቶ አባይ እነዚህ ጥያቄዎች እና የአዲሱ ትውልድ ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱ እንደ አዎንታዊ እና እንደ ህገ መንግስቱ ቱርፋት የመቆጠራቸውን ያህል፥ ህገ መንግስቱ ያስቀመጣቸውን ግዴታዎችን አለመፈፀም የወቅቱ ስጋት መሆናቸውን አንስተዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር ወንድወሰን በበኩላቸው ህገ መንግስቱ በአግባቡ እንዲከበር እና ሳይሸራረፍ ተግባራዊ ሆኖ እንዲጓዝ፥ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በትጋት መስራት አለብን ነው ያሉት።

ለዚህም ሁሉም ዜጎች የሀገሪቱ አንድነት ምስሶ የሆነውን ህገ መንግስት፥ ሳይሸራረፍ ማክበር እና ማስከበር እንዳለባቸው አብራርተዋል።

የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የጥናት ክፍል ባልደረባው አቶ አባይ በበኩላቸው፥ በቅርቡ በዩኒቨርሲቲው ያሉ ታዋቂ ምሁር በሀገራት የሚታዩ የውስጥ አለመግባባቶች እና ዜጎችን ለበርካታ ጥያቄ የሚያነሳሱ የአስተዳደር ችግሮች እና መፍትሄዎች ምንድን ናቸው በሚል ጉዳይ ላይ ጥናት ማካሄዳቸውን ይናገራሉ።

እኝህ ምሁር ለዓለም አቀፋዊ የወቅቱ ጥያቄዎች ቴክኒካዊ እና ባህሪያዊ ለውጥ የሚያመጡ ሁለት የአስተዳደር ችግሮችን አስቀምጠዋል።

ቴክኒካዊ ችግሮች በቴክኒካዊ ምላሾች የሚፈቱ ሲሆን፥ ለአብነት ያህል የክልሎች የበጀት ጥያቄ በፌደራሉ የበጀት ክፍፍል ቀመር የሚፈታ ነው።

ባህሪያዊ ለውጥ የሚያመጡ ችግሮች ግን አሁንም ለበርካታ ሀገራት መንግስታት ፈተና ሆነው እየተጓዙ ነው ተብሏል።

አቶ አባይ በኢትዮጵያ ውስጥ ባህሪያዊ ለውጥ የሚያመጡ ምላሾች የሚያስፈልጓቸው ጥያቄዎች መኖራቸውን ያነሳሉ።

ለአብነትም በየአካባቢው እየተነሱ የሚገኙ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት መጓደል ይጠቀሳሉ ነው ያሉት።

ለእነዚህ ወቅታዊ ጥያቄዎች የሚሰለቹ እና ተደጋጋሚ ምላሾች ሳይሆኑ የባህሪ ለውጥ የሚያመጡና ወቅቱን መሰረት ያደረጉ ምላሾች መስጠት ያሰፈልጋል የሚል ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል።

ምሁራኑ ሀገሪቱ እያስመዘገበች ያለችው የምጣኔ ሀብት እድገት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በህገ መንግስቱ የተቀመጡ መብቶች እና ግዴታዎች ሳይሸራረፉ በእኩል ደረጃ ተግባራዊ እንዲሆኑ በልዩ ትኩረት እንዲሰራ አስተያየታቸውን አስቀምጠዋል።

 

 

 

 

በስላባት ማናዬ