በሊቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የባሪያ ንግድ ሰለባ እንዳይሆኑ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 28፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በሊቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እየተፈፀመ ባለው የባሪያ ንግድ ሰለባ እንዳይሆኑ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በሊቢያ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሚኖሩባቸው ቦታዎችም መለየታቸውን ገልጿል።

ዜጎቹን ወደ ሀገራቸው ለመመለስም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም በመግለጫቸው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ መንግስትም ካይሮ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አማካኝነት ምን ያህል ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙ፥ መረጃ የማሰባሰብ ስራዎች እየሰራ መሆኑን አቶ መለስ ጠቁመዋል።

በቀጣይም ለዜጎቹ የጉዞ ሰነድ የመስጠት እና ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የማድረግ ስራዎች ይሰራሉ ተብሏል።

በሊቢያ ቢያንስ 20 ሺህ የሚጠጉ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የሄዱ ስደተኞች በመንግስት እስር ቤቶች ውስጥ ይገኛሉ።

በሊቢያ አፍሪካውያኑ ስደተኞች በጨረታ ለግለሰቦች እንደሚሸጡ የሚያሳዩ ዘገባዎች መውጣታቸውን ተከትሎ በዚያች አገር የሚገኙ ስደተኞች ያሉበት ሁኔታ ዓለም አቀፍ ትኩረትን ስቧል።

በቅርቡ በተካሄደውም የአፍሪካ እና አውሮፓ ህብረቶች የጋራ ጉባኤ ላይ እነዚህን ስደተኞች ወደየአገራቸው ለመመለስ ከስምምንት መደረሱ ይታወቃል።

በሌላ በኩል ቃል አቀባዩ እስከ ህዳር ወር 2010 ዓ.ም በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ 10 ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የጉዞ ሰነድ መውሰዳቸውን ገልፀዋል።

በአጠቃላይ እስከአሁን 130 ሺህ ኢትዮጵያውያን የጉዞ ሰነድ የወሰዱ ሲሆን፥ ሰነድ ከወሰዱት ውስጥም 70 ሺህ የሚሆኑ ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ተጠቁሟል። 

 

 

በዙፋን ካሳሁን