ሩሲያ በሶሪያ የሚገኘው አይኤስ ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን ገለፀች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 28፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ ጠቅላይ ጦር ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ቫሌሪ ጌራሲሞቭ በሶሪያ የሚገኘው አይኤስ ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን ገልፀዋል።

ኢታማዦር ሹሙ ትናንት ሩሲያ በውጭ ሀገራት በምትሰራቸው ወታደራዊ ስራዎች ዙሪያ በሞስኮ በሰጡት ማብራሪያ፥ በሶሪያ የሚገኙ ሁሉም የሽብር ቡድኑ ክንፍ መደምሰሱን እና በይዞታው ስር የነበሩ ግዛቶችም ነፃ መውጣታቸውን ተናግረዋል።

ጀኔራል ጌራሲሞቭ ዛሬ ላይ በአይኤስ የተያዘ ምንም አይነት ቦታ በሶሪያ ውስጥ የለም ነው ያሉት።

አይኤስ በስሩ የነበረችውን የመጨረሻዋን ግዛት ዴር ኤዝ ዞውር በቅርቡ መነጠቁ ይታወሳል።

የሩሲያው ጠቅላይ ጦር ኢታማዦር ሹም፥ በኢራቅ አይኤስን ለመደምሰስ በሚደረገው ጥረት ሀገራቸው በአሜሪካ የሚመራውን ጥምር ሃይል እንደምተቀላቀልም አንስተዋል።
ሶሪያ ከፈረንጆቹ 2011 ጀምሮ በማያቋርጥ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ቆይታለች።

ባለፉት ስድስት ዓመታትም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች የሞቱ ሲሆን፥ ከ10 ሚሊየን በላይ ዜጎች ደግሞ መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ ያሳያል።

ምንጭ፦አናዶሉ