የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ሲምፖዚየም በሰመራ ከተማ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 28፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የ12ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ክብረ በዓል በህገ መንግስት አስተምህሮዎች ላይ የሚያተኩር ሲምፖዚየም በሰመራ ከተማ ዛሬ እየተካሄደ ነው፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ያለው አባተ በሲምፖዝየሙ ላይ ባሰሙት የመክፈቻ ንግግር፥ እየተመዘገበ ያለውን እድገት ለማስቀጠል የህገ መንግስት አስተምህሮ ስራን በላቀ ደረጃ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

አፈ ጉባኤው የሀገሪቱ ህዝቦች ህገ መንግሰቱን ሊረዱ እና ሊተገብሩ ይገባል ሲሉም ገልጿል።

በሲምፖዚየሙ ላይ የመወያያ ፅሁፍ ያቀረቡት የኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የብአዴን ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አለምነው መኮንን በበኩላቸው፥ የቋንቋ፣ የሀይማኖት እና የባህል ልዩነትን አቻችሎ ለማስኬድ ብቸኛ መፍትሄው የዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት አስተሳሰብን ማጎልበት መሆኑን ገልፀዋል። 

አቶ አለምነው መኮንን ህብረ-ብሔራዊነት በስፋት በሚታይባቸው ሀገራት ህዝቦችን አቻችሎ በመከባበር የሚኖሩበትንና በአስቸጋሪ ሁኔታም ሳይቀር ዘላቂውን የጋራ እድገት እና አብሮነት እያዩ የሚዘልቁበትን ሁኔታ ማረጋገጥ ይጠይቃል ነው ያሉት።

ይህ ከባድ ስራ ሊሳካ የሚችለው ደግሞ በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ የአስተሳሰብ እና የማንነት ብዝኃነትን አሟልቶ በመረዳት መሆኑንም አብራርተዋል።

በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች ያለው ሀገር ግንባታ ያለ እንከን ሊፈፀም አይችልም ያሉት አቶ አለምነው፥ ዘላቂ መፍትሄ የሚሆነው ልዩነቶችን በማቻቻል አንድነትን የማጎልበት ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

ዴሞክራሲያዊነትን የተላበሰ ህብረ ብሄራዊ አስተዳደርን አጠናክሮ በማስቀጠል የዜጎችን ጥያቄ መመለስ እንደሚቻልም አብራርተዋል፡፡

በፓናል ውይይቱ ላይ ህብረ ብሄራዊነት እና ፌደራሊዝም ለሀገራችን የህዳሴ ጉዞ ተስፋ መሆናቸውም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ይህን ተስፋ አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚያስችልም የመወያያ ፅሁፍ አቅራቢው አንስተዋል።

ብሔራዊ ማንነትን ጠብቆና ተንከባክቦ ትልቅ ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ሂደት የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ልሂቃኑን ሚና የዳሰሱት አቶ አለምነው፥ በሀገር ግንባታው ሂደት መሪ ተዋናይ መሆን ያለበት ግን ሰፊው ህዝብ ነው ብለዋል፡፡

ዴሞክራሲ እና ፌዴራሊዝም ሊነጣጣሉ የማይችሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች መሆናቸውን ነው ያነሱት።

ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የቋንቋ፣ የባህል፣ የስነ-ልቦና፣ የኃይማኖት እና ተጓዳኝ ልዩነት አለን ብለው የሚያምኑ በአንድ ሀገር የሚኖሩ ህዝቦችን አስማምቶ ማልማትና ማሳደግ የሚችል ብቸኛ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አማራጭ ነው ማለታቸው ተገልጿል፡፡

በቀረበው ፅሁፍ ላይ ውይይት እየተደረገ ሲሆን፥ በውይይቱም የብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮች፣ የፌዴራል እና የክልል አመራሮች፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡