የፀጥታው ምክር ቤት በኢየሩሳሌም ጉዳይ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ ሊያካሂድ ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 28፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሃገራቸው ለእየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማነት በይፋ እውቅና መስጠቷን ይፋ ማድረጋቸው ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ነገ አስቸኳይ ስብሰባውን በጉዳዩ ላይ ሊያካሂድ ነው።

በተመድ የፈረንሳይ ልኡክ በትዊተር ገፁ ባሰፈረው መረጃ፥ ፈረንሳይ ከቦሊቪያ፣ ግብፅ፣ ጣሊያን፣ ሴኔጋል፣ ስዊድን፣ ብሪታንያ እና ኡራጓይ ጋር የፀጥታ ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲያካሂድ ጠይቃለች ብሏል።

የፈረንሳይ የልዑካን ቡድን ቃል አቀባይ አይሜሪክ ቹዜቪሌ እንደገለፁት፥ ስብሰባው የሚካሄደው ዓርብ ጧት ነው።

በተባበሩት መንግስታት የቦሊቪያ ልኡክ የፀጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ጥያቄን አረጋግጧል።

ፈረንሳይ ዩናይትድ ስቴትስ በኢየሩሳሌም ላይ የሰጠችው ውሳኔ መቃወሟ ይታወሳል።

የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደገለፀው ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሀገራቸው እስራኤል እና ፍሊስጤም በሰላም እና በደህንነት እንዲኖሩ ኢየሩሳሌም የሁለቱም ሀገራት ዋና ከተማ ሆና መቀጠሏን እንደምትደግፍ ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቱ በዚህ ጉዳይ ላይ መረጋጋት እና ውይይትን እንደሚመርጡም አስታውቀዋል።

በተመድ የአሜሪካ ቋሚ መልዕክተኛ ኒኪ ሀሌ በበኩላቸው፥ የትራምፕ ውሳኔ ትክክልኛ እና ታሪካዊ ነው ብለውታል።

የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማ እንድትሆን እውቅና እንዳልሰጠም ተነግሯል።

የኢየሩሳሌም ጉዳይ ለረዥም ጊዜ ያልተፈታ ችግር ሲሆን፥ የአሁኑ የትራምፕ ውሳኔ በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ ብጥብጥ ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

 

ምንጭ፦xinhuanet.com