ጣሊያን ለኢትዮጵያ ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ስራ የ1 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አደረገች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 28፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ጣሊያን ለኢትዮጵያ ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ስራ የ1 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አድርጋለች።

የድጋፍ ስምምነቱን በጣሊያን የልማት ትብብር ኤጀንሲ የአዲስ አበባ ቢሮ ዳይሬክተር ሚስ ጊኔቭራ ለቲዚያ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) የኢትዮጵያ ተወካይ ሚስ ጊሊያን ሜልሶፕ በአዲስ አበባ ፈርመዋል።

820 ሺህ ሕጻናትን ተጠቃሚ የሚያደርገው የፕሮጀከት ስምምነቱ ለአንድ ዓመት የሚቆይ ሲሆን፥ ድጋፉ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ በተለይ የህጻናት ልደት ምዝገባን ለማጠናከር ያለመ ነው።

የኦሮሚያ ክልል የወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መርድ ጉደታ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ፕሮጀክቱ የባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት፣ መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግና ተያያዥ ስራዎችን ለማዘመን ያግዛል።

ጣሊያን ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው አጠቃላይ የልማት ስራዎች ድጋፍ ከሚያደርጉ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት መካከል ከቀዳሚዎቹ መካከል ተጠቃሽ ሀገር ናት።

ሀገሪቱ የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) አጋር አካላት ፎረም የጋራ ሊቀመንበር ስትሆን፥ በፎረሙ ለሚከናወኑ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች ተፈጻሚነት ድጋፍ በማድረግ ላይ ናት።

ከ300 ሚሊየን ዩሮ በላይ የንግድና ኢንቨስትመንት ልውውጥ ያላቸው ኢትዮጵያና ጣሊያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ከጀመሩ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ሆኗቸዋል።

ሀገራቱ በኢትዮጵያ የተቀናጀ፣ ሁሉን አቀፍና ዘላቂ ልማት ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ዓላማ ያደረገና ለሶስት ዓመት ተግባራዊ የሚደረግ የ125 ሚሊየን ዩሮ የልማት ትብብር ስምምነት በያዝነው ዓመት መስከረም ወር መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።

 

 

 

 

 

 

 

ምንጭ፦ኢዜአ