አሜሪካ ለእየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማነት እውቅና ሰጠች

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 27 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ለእየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማነት በይፋ እውቅና ሰጠች።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዛሬ በዋሽንግተን በሰጡት መግለጫ፥ ሃገራቸው ለእየሩሳሌም ዋና ከተማነት እውቅና መስጠቷን ይፋ አድርገዋል።

አሜሪካ በፈረንጆቹ 1995 በእስራኤል የሚገኘው የሃገሪቱ ኤምባሲ ከቴል አቪቭ ወደ እየሩሳሌም እንዲዛወር ህግ ማውጣቷ የሚታወስ ነው።

ይሁን እንጅ ሃገሪቱን የሚመሩ ፕሬዚዳንቶች፥ ህጉ እንዳይተገበር በየስድስት ወሩ በፊርማ ሲያግዱት ቆይተዋል።

ከትናንት በስቲያ ይህን ማድረግ የነበረባቸው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን ፊርማውን ችላ ብለው፥ ከቀድሞዎቹ መሪዎች በተለየ መልኩ ለእየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማነት እውቅና ሰጥተዋል።

ትራምፕም ከቀድሞዎቹ መሪዎች በተለየ መልኩ ይህን ህግ ተግባራዊ ማድረጊያው ጊዜ አሁን ሲሉ ተደምጠዋል።

እውቅና የመስጠት ውሳኔው በአሜሪካ ፍላጎትና ለእስራኤልና ፍልስጤም ሰላም ሲባል የተሰጠም ነው ያሉት በንግግራቸው።

እስራኤልም እንደ ማንኛውም ሉዓላዊ ሃገር መዲናዋን የመወሰን መብት አላት ያሉት ፕሬዚዳንቱ መዲናዋም እየሩሳሌም ናት ሲሉ ተደምጠዋል።

በእስራኤል የሚገኘው የሃገሪቱን ኤምባሲ ከቴል አቪቭ ወደ እየሩሳሌም የማዛወር ሂደቱ እንዲጀመርም አዘዋል።

ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት አደርገዋለሁ ሲሉት የነበረውን አካሄድ ዛሬ ይፋ ማድረጋቸው በርካቶችን አስቆጥቷል።

ፍልስጤማውያንም ትራምፕ ለእየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማነት እውቅና መስጠታቸውን ተከትሎ ተቃውሟቸውን እየገለጹ ነው።

የፍልስጤም አስተዳደርን ጨምሮ በርካታ የዓረብ ሃገራት መሪዎችም የፕሬዚዳንቱን እውቅና መስጠት በጽኑ አውግዘዋል።

ሃገራቱ ለእየሩሳሌም ዋና ከተማነት እውቅና መስጠት፥ የእስራኤል - ፍልስጤም የሰላም ድርድር ላይ እክል ይፈጥራል እያሉ ነው።

የአሁኑን ድርጊትም አሜሪካ ለእስራኤል ህገ ወጥ ሰፈራና ወረራ የምትሰጠውን ድጋፍ ማሳያ ብለውታል።

ሃማስ በበኩሉ እየሩሳሌምን የፍልስጤማውያኑ ቀይ መስመር በማለት፥ በአካባቢው የሚደረግን የእስራኤል መስፋፋት ፍጹም እንደማይደግፍ ገልጿል።

ኋይት ሃውስም በመላው ዓለም ለሚገኙ አሜሪካውያን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።

አሜሪካ ለእየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማነት እውቅና መስጠቷን ተከትሎ ዜጎች ጥቃት ሊሰነዝርባቸው ይችላል በሚል ነው ማስጠንቀቂያው የተሰጠው።

በመላው ዓለም የሚገኙ አሜሪካውያንም ራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳስቧል።

እስራኤል ከፈረንጆቹ 19 67 ጀምሮ በምስራቃዊ እየሩሳሌም በርካታ የሰፈራ መንደሮችን ስትገነባ ቆይታለች።

ይህ ድርጊቷ ግን አለም አቀፉን ማህበረሰብ ጨምሮ፥ እየሩሳሌምን የወደፊቷ መዲናችን ለሚሉት ፍልስጤማውያን የሚዋጥ አልሆነም።

የማያወላዳ የሰላም ስምምነት ተገኝቶለት የማያውቀው የእስራኤል ፍልስጤም ጉዳይ ቀጣይ እጣ ፈንታም አሳሳቢ ሆኗል።

የዛሬው እውቅና በቋፍ ላይ የነበረውን የሰላም ድርድር ገደል እንዳይከተውም ተሰግቷል።