ቭላድሚር ፑቲን ሃገራቸውን ለተጨማሪ ጊዜ መምራት እንደሚፈልጉ ገለጹ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 27 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሃገራቸውን ለተጨማሪ ጊዜ በፕሬዚዳንትነት መምራት እንደሚፈልጉ ገለጹ።

ፕሬዚዳንቱ በመጭው መጋቢት ወር በሚካሄደው የሃገሪቱ ጠቅላላ ምርጫ መሳተፍና አሸንፈው ሃገራቸውን ለተጨማሪ አመታት መምራት እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል።

በዛሬው እለት አንድ ተሽከርካሪ ማምረቻ ፋብሪካን በጎበኙበት ወቅት ነው ሃገራቸውን ለተጨማሪ አመታት የመምራት ፍላጎታቸውን የገለጹት።

በምርጫውም የተሻለ ነገር እንደሚያገኙና እንደሚያሸንፉ ለፋብሪካው ሰራተኞች ገልጸውላቸዋል።

ፕሬዚዳንት ፑቲን በፈረንጆቹ 19 99 በወቅቱ የሃገሪቱ መሪ ቦሪስ የልሲን፥ እንደ ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲያገለግሉ ከተሾሙ በኋላ በቀጣዩ አመት የተካሄደውን ምርጫ አሸንፈው ሩሲያን መምራት ችለዋል።

ከዚያ ጊዜ ወዲህም በፕሬዚዳንትነትና በጠቅላይ ሚኒስትርነት የምስራቅ አውሮፓዋን ሃገር መርተዋታል።

አሁን ለአራተኛ ጊዜ እሳተፍበታለሁ ያሉትን ምርጫ ተሳክቶ ማሸነፍ ከቻሉም ሃገራቸውን ለአራተኛ ጊዜ እስከ ፈረንጆቹ 2024 ድረስ መምራት ይችላሉ ማለት ነው።

በመጋቢቱ ምርጫ የፑቲን ተቀናቃኝ የሆኑት አሌክሲ ናቫልኒ በሙስናና የፓርቲውን ገንዘብ አላግባብ በመጠቀም ወንጀል በመከሰሳቸው አይሳተፉም ተብሏል።

ይህን ተከትሎም ተፎካካሪ አልባ የሆኑት ፑቲን ህገ መንግስቱ ባይፈቅድላቸውም በጠቅላይ ሚኒስትርነትም ቢሆን ሩሲያን ዳግም ሊመሩ ይችላል እየተባለ ነው።

በበርካታ ሩሲያውያን ዘንድ የሚወደዱት ፑቲን በህግ ከተመረቁ በኋላ በሰላይነት እንዲሁም በ19 90ዎቹ ደግሞ የፒተርስበርግ ከንቲባ ከፍተኛ አማካሪ ሆነው ሰርተዋል።

ከዚያም በሃገሪቱ የደህንነት ክፍል ሃላፊነትና ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ከፍተኛውን ስልጣን ለመቆናጠጥ በቅተዋል።

የአሁኑ እቅዳቸው ግን በሌሎች ፖለቲከኞች የተወደደ አይመስልም፤ ሃገሪቱን በብቸኝነት ለመምራት ሌሎችን አላግባብ ይወነጅላሉ ሲሉም ይወቅሷቸዋል ፖለቲከኞቹ።

ፑቲን የእርሳቸው ተቀናቃኝ የሆነን ፖለቲከኛ በሙስናና መሰል ወንጀሎች አስታከው ከመድረኩ ያገላሉ ሲሉም ነው የሚወቅሷቸው።

 


ምንጭ፦ ሬውተርስ እና ቢቢሲ