በግጭቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ17 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የምግብ ድጋፍ ተደርጓል

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 27 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ17 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የምግብ ድጋፍ መደረጉን የብሔራዊ አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተፈጥሮ ሃብት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2010 በጀት ዓመት ዕቅድና የበጀት ዓመቱን የሩብ ዓመት አፈጻጻም ዛሬ አቅርቧል።

ኮሚሽነሩ አቶ ምትኩ ካሳ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፥ በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢ በተከሰተ ግጭት ከ900 ሺህ በላይ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

ለተፈናቀሉትና በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ለተጠለሉ ዜጎችም በመንግስት፣ በህብረተሰቡና በግብረ ሰናይ ድርጅቶች የምግብ፣ የመጠለያና ሌሎች ድጋፎች መደረጉን ገልጸዋል።

ከተረጂዎቹ መካካል 629 ሺህ የሚሆኑት ከኦሮሚያ ክልል ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ናቸው ብለዋል።

መንግስት ለተፈናቃዮቹ ከ48 ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ ምላሽ የሰጠ ቢሆንም፥ በጸጥታና በመሰረተ ልማት ችግሮች ሳቢያ እርዳታውን በፍጥነት የማድረስ ችግር ማጋጠሙን ጠቁመዋል።

የአደጋዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ መበራከት የመንግስትን አቅም እየተፈታተ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፥ ችግሩን ለመፍታት ተረጂዎችን መልሶ በማደራጀት በኩል በሚሰራው ስራ የክልሎች ሚና ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

በቅርቡም በሶማሌና በኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ መኖሪያ ቀያቸው እንዲመለሱና የማደራጀት ስራ ለማከናወን የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተጠናቀቀ መሆኑን አስረድተዋል።

 

 

ምንጭ፦ ኢዜአ