በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ድርቅን በዘላቂነት መቀነስ የሚያችሉ ስራዎች እየተሰሩ ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 27፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በዘላቂ ልማት ድርቅን ለመቀነስና አርብቶ አደሩን የተቀናጀ ለማት ተጠቃሚ በማድረግ ወደ ከፊል አርሶና አርብቶ አደርነት የሚያሸጋግሩ ስራዎች እየተሰሩ ነው።

በክልሉ በሁለት ዞኖች ብቻ 21 ሺህ አባወራ አርብቶ አደሮችን በዓመት ሁለት ጊዜና ከዚያ በላይ እንዲያመርቱ የሚያስችሉ የውሃ ማሰባሰብ ስራዎች እየተሰሩ ነዉ።

ከጋዜጠኞችና ከሚዲያ ባለሙያዎች የተውጣጣ ቡድን በክልሉ ጀረሮ እና ቆርሃይ ዞኖች በሚገኙ ብርቆድ እና ቀብሪ ደሃር ወረዳዎች ውስጥ የተሰሩ የልማት ስራዎችን ተዘዋውሮ ተመልክቷል።

በእነዚህ አካባቢዎች ከዚህ በፊት በየዓመቱ ለስድስት ወራት ያለ ምንም ጥቅም የጎርፍ አደጋን እያስከተሉ ወደ ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ሲፈሱ የነበሩ ወንዞችን የማቀብ ስራዎች ተሰርተዋል።

ውሃው እያንዳንዳቸው ዘጠኝ ሄክታር ስፋት እና አራት ሜትር ጥልቀት ባላቸው 9 የውሃ ማከማቻ ጉድጓዶች (ፖድ) ውስጥ ነው የተከማቸው።

እንዳንዳንዱ ጉድጓድም ከ270 ሺህ እስክ 300 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃን መያዝ የሚችል ሲሆን፥ 21 ሺህ ሄክታር መሬትን ማልማት የሚችሉ ናቸው።

et_som_water_2.jpg

በአሁኑ ወቅትም 11 ሺህ አባወራ አርብቶ አደሮች ውሃው ባለበት አካባቢ የተለያዩ ሰብሎችን እና አትክልቶችን በማምረት ላይ ይገኛሉ።

ከዚህ በተጨማሪም አርብቶ አደሮቹ ውሃውን ለመጠቀም በመንደር መሰባሰባቸው፥ የጤና፣ የትምህር እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

እስካሁን ያመረቱት ምርትም መነሳሳትን እንደፈጠረላቸው አርብቶ አደሮች ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አብዲ አወል፥ ውሃውን ከማከማቸት ጎን ለጎን አርብቶ አደሩ በዚህ ስራ ላይ እንዲሰማራ የማማከር እና የማሳመን ስራ ተሰርቶ ውጤታማ መሆን ተችሏል ብለዋል።

ከዚህ ልምድ በመቅሰምም የአርብቶ አደሩን ኑሮ የሚያሻሽሉ ስራዎችን በሌሎች ዞኖች እና ወረዳዎች በቀጣይነት እንደሚሰራም አስረድተዋል።

በብዙአለም ቤኛ