ከ16 ሺህ በላይ የስራ መደቦች የስራ ምደባና የደረጃ አወሳሰን ተዘጋጅቶ መጠናቀቁ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 27፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከ16 ሺህ በላይ የስራ መደቦች የስራ ምደባ እና የደረጃ አወሳሰን ተዘጋጅቶ መጠናቀቁን የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚንስትሩ አቶ ታገሰ ጫፎ ተናግረዋል።

ምዝናው በ476 የፌደራልና የክልል የመንግስት ተቋማት የተከናወነ ሲሆን፥ የተመዘኑ ስራዎች ከደረጃ አንድ እስከ 22 ባለው መደብ ተቀምጠዋል።

አዲሱ የስራ ምዘና አወሳሰን በተሰራላቸው የስራ መደቦች ላይ የስራ ዝርዝር የማዘጋጀት ስራውም ተጠናቋል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

ይህ አሰራር አንድ ሰራተኛ በሚሰራው ስራ እኩል ክፍያ እና ተገቢውን ጥቅማጥቅም እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን ነው የተናገሩት።

አቶ ታገሰ እንደተናገሩት፥ የፊታችን ታህሳስ ወር ቀሪ ስራዎችን በማጠናቀቅ አሰራሩ በጥር ወር ወደ ተግባር ይገባል።

የመንግስት ሰራተኞች የስራ ምዘና እና የደረጃ አወሳሰን ከሚያዝያ ወር 2008 ዓ.ም ጀምሮ በሙከራ ደረጃ መተግበር ይጀምራል ተብሎ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ተጠናቆ ወደ ስራ መግባት አልቻለም።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከዚህ ቀደም የመንግስት ሰራተኞች የስራ ምዘና እና የደረጃ አወሳሰን ፕሮጀክት በ2009 ዓ.ም በሁሉም ተቋማት ይጀመራል ብሎ እንደነበር ፋና ብሮክካስቲንግ ኮርፖሬት መዘገቡ የሚታወስ ነው።

ብዙ መዘግየቶች የታዩበት ሰራተኞች የስራ ምዘና እና የደረጃ አወሳሰንን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እስካሁን ተግባራዊ ማደረግ አልተቻለም።

በገንዘብ አወቀ